ዜናህግ እና ፍትህ

ዜና: በሀሰተኛ የክፍያ ሰነድ 6 ሚሊየን 50 ሺህ ዶላር ዝውውር ወንጀል ተጠርጥረው ለእስር የተዳረጉት ቀሲስ በላይ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16/2016 ዓ.ም፡- ከአንድ ሳምንት በፊት በአፍሪካ ህብረት ቅጥር ጊቢ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአካል ቀርበው ሀሰተኛ የክፍያ ሰነዶችን በመያዝ ለ3 ግለሰቦች እና ለአንድ የግል ድርጅት ሂሳብ 6 ሚሊየን 50 ሺህ ዶላር ለማዘዋወር በመሞከር ወንጀል ተጠርጥረው ለእስር የተዳረጉት ቀሲስ በላይ መኮንን በተጠረጠሩበት ወንጀል ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት መቅረባቸው ተገለጸ።

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የቀሲስ በላይ መኮንንን ጨምሮ የ3 ግለሰቦችን ጊዜ ቀጠሮ መዝገብን ዛሬ ሚያዚያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ መመልከቱን ከፋና ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ፍርድ ቤቱ በቀሲስ በላይ መኮንን፣ ያሬድ ፍስሃ እና ጣባ ገናና በተባሉ 3 ተጠርጣሪዎች ላይ ለምርመራ ማጣሪያ ለፖሊስ በሰጠው 7 ቀን የምርመራ ጊዜ ውስጥ የተከናወኑ ስራዎችን ተመልክቷል።

መርማሪ ፖሊስ በተሰጠው የ7 ቀን ጊዜ ውስጥ የምስክሮችን ቃል መቀበሉን፣ በተጠርጣሪዎች እጅ ላይ የተገኘ ኤሌክትሮኒክስ ምርመራ እንዲደረግ ለሚመለከተው ተቋም መጠየቁን፣ የቴክኒክ ምርመራ እንዲሰጠው በደብዳቤ መጠየቁን አስታውቋል።

በተጨማሪም ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለአፍሪካ ህብረት የሰነድ ማስረጃዎች እንዲሰጠው መጠየቁን፣ ተጠርጣሪዎቹ በስማቸው የሚገኙ ሂሳቦችን ለማጣራት ማረጋገጫ እንዲሰጠው በደብዳቤ መጠየቁን፣ በወቅቱ የነበረ የካሜራ ቅጂ መጠየቁን፣ ለወንጀል ተግባር የዋለ ተሽከርካሪ ማረጋገጫ ከሚመለከተው ተቋም መጠየቁን፣ በቀሲስ በላይ ሁለት መኖሪያ ቤቶች ላይ ብርበራ ማድረጉንና በብርበራ የተገኘ የጦር መሳሪያ ህጋዊነት የማረጋገጥ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

ቀረኝ ያላቸውን ስራዎችን ማለትም ከተለያዩ ተቋማት የሰነድ ማስረጃ መሰብሰብ፣ ተጨማሪ ምስክሮችን ቃል መቀበል፣ ግብረአበሮችን ተከታትሎ መያዝ፣ ተጨማሪ ሀብት የማፍራት ተግባሮች ላይ የማጣራት ስራ መስራት እንደሚያስፈልገው አስታውቋል።

በተቀናጀና በቡድን የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት ጥላሸት የሚቀባ ተግባር መሆኑን ጠቅሶ ምርመራውን በተጠናከረ መንገድ በስፋት ለማከናወን ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ገልጾ መርማሪ ፖሊስ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ተጠርጣሪው ቀሲስ በላይ መኮንንን ጨምሮ ሌሎቹም ተጠርጣሪዎች በ6 ጠበቆች ተወክለው ችሎት የቀረቡ ሲሆን ጠበቆቻቸው ፖሊስ ያቀረበው ጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ምክንያቶች ደንበኞቻቸውን ተጨማሪ በእስር ለማቆየት የሚያስችል አይደለም በማለት ተከራክረዋል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን የተመለከተው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ተጠርጣሪው ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው በማለፍ ለፖሊስ የ8 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ፈቅዷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button