ዜናፖለቲካህግ እና ፍትህ

ዜና፡ አቶ ታዬ ደንደአ “የፀረሰላም ኃይሎችን በመደገፍ እና የጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘት" ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 17/ 2016 ዓ/ም፦ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ተከትሎ በጸጥታ ሀይሎች ታህሳስ 2 ቀን በቁጥጥር ስር የዋሉት የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ታዬ ደንደኣ “የፀረሰላም ኃይሎችን በመደገፍና ጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘት” ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው። 

ክሱ የተመሰረተው በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሕገ-መንግስትና ሕገ-መንግስት ሥርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮችን በሚመለከተው ችሎት ሲሆን፤ የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሽ ታዬ ደንደአ ላይ ሶስት ክሶችን አቅርቧል።

በዚህም መሰረት በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 251/ሐ እና አንቀጽ 257/ሰ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ እና የጦር መሳሪያ አዋጅን መተላለፍ የሚል ክስ አቅርቦባቸዋል።

በክሱ ላይ እንደተመላከተው፤ “ተከሳሹ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ሆነው ሲሰሩ የሀገርን፣ የመንግስትንና የህዝብን ደህንነት ማረጋገጥ ሲገባቸው ይህን ወደጎን በመተው  ፀረሰላም ኃይሎችን የሚደግፉ የፕሮፖጋንዳ መልዕክቶችን በማስተላለፍ በስማቸው በተከፈተ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ድጋፍ የሚገልጹ መልዕክቶችን  ሲያስተላልፉ ነበር” የሚል ነው፡፡

እንዲሁም ፍቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሳሪያ አዋጁን በመተላለፍ በታህሳስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም  ከረፋዱ 5 ሰዓት  ላይ በልደታ ክ/ከ ወረዳ 6  በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በተደረገ ብርበራ አንድ ታጣፊ ክላሽን ኮቭ  መሳሪያ ከ2 ክላሽ ካዝና  እና ከ60 ጥይት ጋር ይዘው መገኘታቸው ተጠቅሶ ክስ ቀርቦባቸዋል።

አቶ ታዬ ደንደኣ በቁጥጥር ስር ሲውሉ በራሳቸው እና በቤተሰባቸው ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደደረሰባቸው ገልጸው አቤቱታ በቃል አቅርበዋል። ምርመራው ታሕሳስ 24 ማለቁንና ዘግይቶ ክስ መቅረቡንም ተቃውመዋል።

ዐቃቤ ሕግ ሌሎች ምርመራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልጾ መልስ ሰጥቷል ሲል ፋና ዘግቧል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ፍርድ ቤቱም በአያያዝ ላይ ያቀረቡትን የመብት ጥያቄ በሚመለከት በጽሑፍ በዝርዝር ማቅረብ እንደሚችሉ ገልጾ፤ ዋስትናውን በሚመለከት መርምሮ ብይን ለመስጠትም ለሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

አቶ ታዬ በማህበራው ትስስር ገጻቸው በተደጋጋሚ መንግስትን ሲተቹ የሚስተዋሉ ሲሆን በቅርቡ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ “በመንግስት እና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል የተካሄደው የሰላም ድርድር ላለመሳካቱ ምክንያት መንግስት ነው” በማለት መናገራቸው ይታወሳል። ይህንን ተከትሎ ጠ/ሚ አብይ አህመድ ከታህሳስ 1 ጀምሮ አቶ ታዬን ከሃላፊነታቸው አንስተዋል።

በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ይፋ ያደረገው የፀጥታና ደኀንነት የጋራ ግብረ ኃይል፤  “በመንግስት ቁጥጥር ስር ሊዉሉ እንደሚችል ሲገምት ታጋይ ለመምሰል በራሳቸውና በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች አፍራሽና ፀረ ሰላም ፅሁፎችን፣ ንግግሮችንና መግላጫዎችን በማን አለብኝነት ሲያስተላልፉና ሲሰጡ በመቆየታቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል” በሏል።

የቀደሞው የሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንዳኣ ባለቤት ወ/ሮ ስንታየሁ አለማየሁ በወቅቱ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ ባላቤታቸው በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ መንግስት ከሰጣቸው መኖሪያ ቤት ለቀው እንዲወጡ መደረጋቸውን ገልጸዋል። 

በፍተሻው ወቅት በቤታቸው ውስጥ ተገኝተዋል የተባሉትን የጦር መሳሪያና ሌሎች እቃዎችን በተመለከተ እና “ከፀረ-ሰላም አካላት ጋር በመንግስት እና በፓርቲያቸው ላይ አሲረዋል” ሲል መንግስት ያቀረበባቸውን ውንጀላ በተመለከተ ወ/ሮ ስንታየሁ “ተቀባይነት የለውም” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button