ዜናፖለቲካህግ እና ፍትህ

ዜና፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚፈፀሙ የጋዜጠኞች እስር አሳስቦኛል፤ መንግስት የታሰሩ ጋዜጠኞችን በሙሉ  ይፍታ- ሲፒጄ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 2/ 2015 .ም፡ አለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄ ትላንት ረቡ ጳጉሜ 1፣ 2015 ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በሳምንታት ውስጥ የተፈፀሙ የጋዜጠኞች እስር እንዳሳሰበው ገልፆ በስራቸው ምክንያት የታሰሩ ጋዜጠኞችን በሙሉ መንግስት በአስቸኳይ እንዲፈታ ጠይቋል፡፡

ላለፉት አራት አመታት በኢትዮጵያ በተለይ በፖለቲካ ውጥረት እና ግጭት ወቅት ተደጋጋሚ የጋዜጠኞች እስር ይከናወናል ያለው ሲፒጄ በቅርቡ በአማራ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት ሳቢያ በታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አባይ ዘውዱ፣ ይድነቃቸው ከበደ እና ፍቃዱ ማህተመወርቅ ለእስር ተዳርገዋል ሲል አስታውቋል፡፡

ጋዜጠኞቹ ለእስር የተዳረጉት በአማራ ክልል ስላለው ግጭት እና አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመዘገባቸው መሆኑን ሲፒጄ ተረድቷል ሲል መግለጫው ገልጧል፡፡

የአማራ ሚዲያ ማዕከል የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ዋና አዘጋጅ የሆነው አባይ ዘውዱ ነሐሴ 04/2015 ዓ.ም. በፌደራል ፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ውሎ ነሐሴ 15/ 2015 ዓ.ም ወደ አዋሽ አርባ መወሰዱን ቤተሰቦቹ እና ኢሰመኮ አስታውቋል ሲል ተቋሙ ገልጧል፡፡ ፌዴራል ፖሊስ ለአባይ ዘውዱ በምን ምክንያት በቁጥጥር ስር እንዳዋሉት እንዳልገለፁለት እና ፍርድ ቤት አለመቅረቡን እህቱ ዞማ ዘውዱ ነገራኛለች ንው ያለው፡፡

አፍሪ ነጋሪ የተሰኘ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን መስራች የሆነው ይድነቃቸው ከበደ ሀሙስ ነሃሴ 11 ቀን ከመኖሪያ ቤቱ ተይዞ ለእስር መዳረጉን ገልጧል፡፡ ይድነቃቸው ነሃሴ 15 ፍርድ ቤት ቀርቦ ፖሊስ “ፀረ-ሰላም አካላትን” በመርዳት እና “አመፅን ለማነሳሳት” ቪዲዮዎችን በመስራት ወንጀል እንደጠረጠረው ጠበቃው ሄኖክ አክሊሉ ነግሮኛል  ብሏል፡፡ በድጋሜ ነሃሴ 26 ፍርድ ቤት ቀርቦ በ6000 ብር ዋስ ተፈቷል ሲል ጠበቃውን ጠቅሶ ገልጧል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ የጊዮን መፅሔት ዋና አዘጋጅ ፍቃዱ ማህተመወርቅ ነሃሴ 19 በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን እና ፍርድ ቤት አለመቅረቡን ነገር ግን ነሃሴ ነሃሴ 29 ያለ ክስ ከእስር መለቀቁን ባለቤቱ ህይወት ሀይለገብርዔል ገልፃልኛለች ሲል ሲፒጄ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“አሁንም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ህዝቡ በተለያዩ ግጭቶች ዙሪያ የተለያዩ ዘገባዎችን እና አስተያየቶችን ማግኘት በሚፈልግበት ጊዜ በጋዜጠኞች ላይ እያነጣጠረ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት በስራቸው የታሰሩትን ጋዜጠኞች በሙሉ መፍታት አለባቸው እና አማራ ክልል የታወጀው  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመገናኛ ብዙኃንን ለማፈን እንደማይውል ማረጋገጥ ይገባል።” ሲሉ ከሰሃራ በታች የሲፒጄ ተወካይ ሙቶኪ ሙሞ ተናግረዋል፡፡ አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button