ዜናፖለቲካ

ዜና: በሶማሌ ክልል በእስር የሚገኘው ጋዜጠኛ ሞሀዲን መሐመድ በአስቸኳይ እንዲፈታ ሲፒጄ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4/2016 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት በሶማሌ ክልል በእስር የሚገኘው ጋዜጠኛ ሞሀዲን መሐመድ በአስቸኳይ እንዲፈቱት የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ተቋም ሲፒጄ ጠየቀ።

ጋዜጠኛ ሞሀዲን መሐመድ የሀሰት መረጃ በማሰራጨት ወንጀል በመከሰሱ እስከ አምስት አመት የሚደርስ እስር ሊፈረድበት ይችላል ሲል ስጋቱን አስታውቋል።

ከዚህ ቀደም በካልሳን ቴሌቪዥን፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ  በማህበራዊ ሚዲያ ጦማሪነት እየሰራ የሚገኘው ሞሀዲን፤ በቅርቡ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጅግጅጋ ከተማ መሄዳቸውን ተከትሎ “የአሳቸው መምጣት የትራፊክ መጨናነቅ አስከትሏል” በማለት በማህበራዊ ትስስር ገጹ በመለጠፉ ለዕስር መዳረጉን የሶማሌ ጋዜጠኞች ማህበር ሊቀመንበር አብዱልርዛቅ ሀሳን ዋቢ በማድረግ መዘገባችን ይታወሳል።

ጋዜጠኛ ሞሀዲን ያለ ምንም ክስ ለሰባት ቀናት ባልታወቀ እስር ቤት ታስሮ መቆየቱን ሊቀመንበሩ በወቅቱ ለአዲስ ስታንዳርድ የገለጹ ሲሆን ከዛ በኋላ ወደ ፋፋን ዞን ፖሊስ ጣቢያ መተላለፉን፣ የካቲት 12 ፍርድ ቤት በማቅረብ “የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በማሰራጨት” ክስ እንደቀረበበት ማስታወቃቸውን በዘገባችን ተካቷል።

ሲፒጄ መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የመንግስት ባለስልጣንን በፌስቡክ በመተቸቱ ብቻ እንደ ወንጀል በመቁጠር ጋዜጠኛው ላይ ክስ በመመስረት የሶማሌ ክልል ባለስልጣናት የህዝብን ሀብት ከማባከን ሊቆጠቡ ይገባል ሲሉ የተቋሙ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ ሙታኪ ሙሞ መናገራቸውን አመላክቷል፤ የተመሰረተበት የወንጀል ክስ እንዲቋረጥ በማድረግ በፍጥነት እንዲፈቱት የጠየቁት ሃላፊዋ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስለጣናት ጋዜጠኞች የተናገሩት እና የጻፉት ነገር ስላልጣማቸው ብቻ በእስር ቤት የማጎር ባህላቸውን ሊያቆሙ ይገባል ሲሉ መግለጻቸውን አስታውቋል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button