ዜና

ዜና፡ አማራ ክልል የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መራዘሙ ለህዝባዊ ጥያቄ ዘላቂ መፍትሄ እንደማያመጣ የተቃዎሚ ፓርቲዎች ኮከስ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29/ 2016 ዓ/ም፦ ባሳለፍነው ሣምንት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለአራት ወራት መራዘሙን ተከትሎ የተቃዎሚ ፓርቲዎች ኮከስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መራዘሙ ለህዝባዊ ጥያቄ ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም ሲል ተቃወመ፡፡

የተቃዎሚ ፓርቲዎች ኮከስ ዛሬ ጥር 29/2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “ባለፉት አምስት ዓመታት በዋነኛነት በህዝብ ለሚነሱ ህዝባዊ ጥያቄዎች ማፈኛነት የታወጁት በርካታ አስቸኳይ አዋጆች ያለውጤት አልፎም ችግሮችን በማባባስ ወይም ከታቀዱለት በተቃራኒ ውጤት መጠናቀቃቸውን በተደጋጋሚ አይተናል” ሲል ገልጿል፡፡

ባሳለፍነው አመት በሓምሌ ወር በአማራ ክልል መንግሥት ጠያቂነት የታወጀው እና በውስጡ በሌሎች የአገሪቱ ክልሎችም ሊፈጸም እንደሚችል የተገለጸበት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ አይደለም ሊራዘም የተቀመጠለትን ጊዜም እንደማይጨርስ በተደጋጋሚ ተገልጾ ነበር ሲል መግለጫው አስታውሷል። 

ኮከሱ “አዋጁ በአፈጻጸሙ /አተገባበሩ/ የዜጎችን መብትና የህግ የበላይነትን የማስከበር ዓላማ በተቃራኒ የድሮን ጥቃትን በማስደገፍ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ሊገሰሱ የማይገባቸውን ሰብዐዊ መብቶች በመደፍጠጥ የህዝብ ተወካዪችን ጨምሮ ከፍተኛ በደልና ግፍ አስመዝግቧል” ብሏል።  ለህዝብ ጥያቄና ብሶት ምላሽ መስጠት ባለመቻሉም ተራዝሟል ሲል ገልጿል፡፡  

በመሆኑም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም አንዳችም የተለየ መፍትሄ እንደማያመጣ ያገለጸው ኮከሱ ገዢው ፓርቲ/መንግስት/ “ከተያያዘው አፍራሽ መንገድ ተመልሶ ራሱን ለሃቀኛ አሳታፊና አካታች ዘላቂ የጋራ መፍትሄ እንዲያዘጋጅ” ሲል ጥሪ አቅርቧል። 

በሀገሪቱ ሥር ለሰደዱና በየወቅቱ ለሚከሰቱ የፖለቲካ ችግሮችና ለሚነሱ ጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሄው አካታች፣ አሳታፊ፣ በተዓማኒ ተቋም የሚመራ ፣ የህግ የበላይነት ላይ የተመሰረተ ግልጽ የብሄራዊ መግባባትና ዕርቅ የውይይትና ድርድር መድረክ እንጂ የኃይል እርምጃ አለመሆኑን አመላክቷል። 

የኮከሱ መግለጫ ከዚህ ውጪ ያለው “የማስመሰልና አጀንዳ ማስቀየሻም ሆነ ለድጋፍ ማጋበሻ የገጽታ ግንባታ የታለመ ፕሮፖጋንዳ ከጊዚያዊ የዕለት ውጥረት ማስታገሻነት አልፎ ለህዝብ ጥያቄ ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም፣ ህዝባዊ ትግሉን ያባብሰዋል እንጂ አፍኖ አያስቀረውም” ሲል አሳስቧል፡፡ በተጨማሪም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ከህዝብ ጎን ቆመው አዎንታዊ ተጽዕኖ እንዲሳርፉም ተጠይቋል። አስ 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button