ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ መንግስት ግጭቶች እንዲፈታ እና ለቀረቡ የሠራተኞች ጥያቄ ላይ መፍትሄ እርምጃ እንዲወስድ ኢሰማኮ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 21/ 2016 ዓ/ም፦ መንግስት በአገሪቱ ያሉ ግጭቶችን በዉይይት እንዲፈታ እና የሠራተኞች ጥያቄን እና የሥራ ግብር እንዲቀነስ ለቀረበው ጥያቄ የመፍትሄ እርምጃ እንዲወስድ ኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) ጠየቀ።

ኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ይህን የጠየቀው ሚያዚያ 23 ቀን “ለሠላም መፍትሔ እንሻለን” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀንን (ሜይዴይ) አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ነው።  

“በአገሪቱ በተከሰተው የእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት ምክንያት ሠራተኞች ሕይታቸውን አጥተዋል” ያለው ኮንፌዴሬሽኑ፤ “ከሚሠሩበት የሥራ ቦታ (አካባቢ) ተወስደው ታግተዋል፣ ከሚሠሩበትና ከሚኖሩበት አካባቢም ተፈናቅለዋል እንዲሁም የሚሠሩበት ድርጅትም በመውደሙ ምክንያት የሥራ ዋስትናቸውን አጥተዋል” ሲል ገልጿል። 

በትግራይ ክልል በተከሰተው ጦርነት “የክልሉ ሠራተኞች ላይ የህይወት፣ የአካል፣ የኢኮኖሚና ማኀበራዊ ጉዳቶች ደርሰውባቸዋል” ብሏል፡፡ አክሎም “አሁንም የሚሠሙ ችግሮች ወደዚያ አስከፊ መጠፋፋት እንዳይመጣ ትኩረትን የሚሹ” መሆናቸውን አመላክቷል። 

በተመሳሳይ ሁኔታ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች የሰላም እጦት ችግሮች ምክንያት ጥቂት የማይባሉ ቦታዎች ላይ የልማት ተቋማትና  ሠራተኞች ተረጋግተው በመስራት ላይ አይደሉም ሲል ኮንፌዴሬሽኑ ገልጿል፡፡ 

መንግስት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ያሉትን ግጭቶችና ጦርነቶች በውይይት መፍትሄ እንዲያገኙ ሆደ ሰፊ በመሆን የአንበሳውን ድርሻ እንዲጫወት፤ በተለይም መንግሥትና ታጣቂ ሀይሎች ፊታቸውን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ለውይይት እንዲያዞሩና ዘላቂ ሰላም መፍትሔ እንዲያመጡ ጥሪ አቅርቧል።

ከዚህ በተጨማሪም ሠራተኞች በኑሮ ውድነቱ ምክንያት አንጻራዊ ሰላም በሰፈነባቸው አካባቢዎች ጭምር “በቀን አንድ ጊዜ እንኳ መብላት የሚሳናቸውና አሰከፊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙና ችግሩ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ መንግሥት ለኑሮ ውዲነቱ  አስቸኳይ  መፍትሔ እንዲሰጥ” ኢሰማኮ ጠይቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ደመወዝ ተከፋይ ሠራተኛው ኑሮ ውድነቱን መቋቋም ስላልቻለ የሥራ ግብር እንዲቀነስልንና በአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ በተደነገገዉ መሠረት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ተግባራዊ እንዲሆንም አሳስቧል። 

በተጨማሪም የሥራ ቦታ የሙያ ደህንነትና ጤንነትን አስመልክቶ የወጡ ሕጎች ተግባራዊ እንዲሆኑ አጥብቀን እንጠይቃለን ብሏል፡፡አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button