ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: ብልፅግና ፓርቲ ‘የሚዲያ ሠራዊት’ አቋቁሞ በሚቃወሙት እና በሚተቹት ላይ ስም ማጥፋት ዘመቻ እንደሚያካሂድ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 11/2016 ዓ.ም፡- በገዢው ብልፅግና ፓርቲ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስር የሚንቀሳቀሱ እና ‘የሚዲያ ሠራዊት’ የሚል መጠሪያ ያላቸው የፓርቲው አባላት፤ መንግሥትን በሚተቹ እና በሚቃወሙ ግለሰቦች ላይ በፌስቡክ በተደረጉ የሐሰተኛ መረጃ እንዲሁም ‘የጥላቻ ንግግር’ ተብለው ሊቆጠሩ የሚችሉ ጽሑፎች እና ምስሎች ሥርጭት ላይ እንደተሳተፉ ቢቢሲ ባደረገው ምርመራ ማረጋገጡን አስታወቀ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወረዳ አመራሮችም በፓርቲው የወረዳ መዋቅሮች ትዕዛዝ፣ በተለይም የመንግሥትን ገፅታ በሰው ሰራሽ መንገድ ለመገንባት ፌስቡክ ላይ በሚደረጉ አሳሳች ዘመቻዎች ላይ እንደሚሳተፉም ምርመራው አሳይቷል።

ቢቢሲ ለዘገባው በአዲስ አበባ ከተማ የወረዳ አመራር፣ የፓርቲ አባል እንዲሁም በከተማዋ እና በፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊዎች እና ባለሙያዎችን ማነጋገሩን አስታውቋል። በከተማዋ ከ500 በላይ የክፍለ ከተማ እና ከ3,500 በላይ የወረዳ አመራሮች እንደሚገኙ ጠቁሟል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሰባት ክፍለ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ የፓርቲው የወረዳ መዋቅሮች በዋትስአፕ እና ቴሌግራም ግሩፖች ውስጥ ለሶሻል ሚዲያ ዘመቻዎች የተለዋወጧቸውን መልዕክቶች መመልከቱንም ቢቢሲ በምርመራ ዘገባው አመላክቷል።

በግሩፖቹ ውስጥ ለወረዳ አመራሮች እና ሚዲያ ሠራዊት አባላት የሚሰጡ ትዕዛዞችን እና አፈጻጸማቸውን መከታተሉን፣ የፌስቡክ ዳታዎችን በመውሰድም መተንተኑን ጠቁሟል።

የፌስቡክ እናት ኩባንያ ሜታ፤ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ “ሐሰተኛ አካውንቶችን” በመጠቀም “በኢትዮጵያ መንግሥት” የፌስቡክ ልጥፎች ላይ “ብዛት ያላቸው አዎንታዊ አስተያየቶች” መሰጠታቸውን በምርመራ እንደደረሰበት ማስታወቁንም በዘገባው አካቷል።

ሜታ፤ በዚህ ድርጊት ላይ በተሳተፉ ሐሰተኛ አካውንት እና ገፆች ላይ እርምጃ መውሰዱን እንደገለጸለት፣ ቢቢሲ ሲከታተላቸው የነበሩ አካውንቶችም እንዲወገዱ ማድረጉን አስታውቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የብልፅግና ፓርቲ በበኩሉ ‘የሚዲያ ሠራዊት’ የሚባል አደረጃጀት “አለመኖሩን” በመግለፅ ለቢቢሲ በሰጠው የፅሁፍ ምላሽ ጉዳዩን ማስተባበሉን ዘገባው አካቷል።

የፓርቲው ዋና ፅህፈት ቤት፤ “በተለይ ‘ሐሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር ተብለው ሊቆጠሩ የሚችሉ ጽሑፎች እና ምስሎች [ተሠራጭተዋል]’ በሚል የተገለጸው ፍጹም ተቀባይነት የሌለው አገላለጽ ነው” ማለቱን ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ አቡነ ጴጥሮስ ከአዲስ አበባ ወደ አሜሪካ መጓዛቸውን ተከትሎ በወቅቱ የተሰራጩ መረጃዎችን ቢቢሲ በማሳያነት አቅርቧል።

በቤተክርስቲያኗ እና በገዢው ፓርቲ መካከል የተፈጠረውን ቅራኔ ተከትሎ “ሰበር መረጃ፤ አቡነ ጴጥሮስ ከሀገር ኮበለሉ”፣ “አሜሪካዊው አቡነ ጴጥሮስ ከሀገር ኮብልለዋል!” እና “ከአሜሪካዊ አቡነ ጴጥሮስ ኩብለላ ጀርባ ያሉ እውነታዎች!” የሚል መግቢያ ያላቸው መረጃዎች በወቅቱ ተሰራጭተው እንደነበር አውስቷል።

ለወረዳዎቹ የሚዲያ ሠራዊት አባላት የተላከው መልዕክት፤ “ይህንን መልዕክት በሁሉም ኢንፎርማል ገጾች በሙሉ በስፋት እንዲሠራጭ በንቃት አስተባብሩ፣ የማይሳተፍ የእኛ መዋቅር እንዳይኖር፣ ሁሉም ይሳተፉ” የሚል ትዕዛዝን የያዘ መሆኑን አስታውቋል።

ቢቢሲ በምርመራ ዘገባው ገዢው ፓርቲ ብልጽግና የመንግሥት እና የፓርቲ “ትርክቶች የበላይነት እንዲኖራቸው” በሚል የአዲስ አበባ የወረዳ መዋቅሮች የመንግሥትን ገፅታ የሚገነቡ ጽሁፍ፣ ምሥል እና ቪድዮዎችን በዘመቻ መልክ በፌስቡክ በተደጋጋሚ ሲያሰራጩ እንደነበር ማረጋገጡንም አመላክቷል።

የአመራሮቹ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ጉዳይ የግምገማ አጀንዳም እንደሆነ በአዲስ አበባ ከተማ የወረዳ አመራር፣ የክፍለ ከተማ ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ እና በከተማ አስተዳደሩ አንድ ቢሮ ውስጥ የሚሠሩ የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ እንደነገሩት ጠቁሟል።

“ለምንድነው ላይክ፣ ሼር የማታደርጉት?” የሚል ጥያቄ ለተሳታፊዎቹ እንደሚያቀርብ፣ የሚዲያ ሠራዊት አባላት ላክይ፣ ኮሜንት እና ሼር ማድረጋቸውን የሚያሳይ “ስክሪን ሻት” እንዲልኩ እንደሚጠየቁ ቢቢሲ በግሩፑ የተደረጉ የመልዕክት ልውውጦችን ዋቢ በማድረግ አስታውቋል።

መንግስትን የሚቃወሙ ጽሁፎችን ባጋሩ የፌስቡክ ገጾች ላይ ‘የሚዲያ ሠራዊቱ’ አባላት ተዘጋጅቶ የተሰጣቸውን ጽሁፎች ኮሜንት እንደሚያደርጉ አረጋግጫለሁ ብሏል።

በመንግሥት እና ፓርቲ የፌስቡክ ገጾች ላይ ተከታይ እና ተሳታፊዎችን የማብዛት ጥረት፤ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሁለት ቢሮዎች ላይክ፣ ኮሜንት እና ሼር የሚያደርጉ ሰዎችን እስከመቅጠር እንዳደረሰ ሁለት የቢሮዎቹ ምንጮች እንደገለጹለት በዘገባው አካቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button