ትጥቅ አንግበው የሚታገሉ አካላት ወደ ሀገራዊ ምክክር መድረክ እንዲመጡ ተጠየቀ፤ ጥበቃ ይደርግላቸዋል ተብሏል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14/2016 ዓ/ም፦ ትጥቅ አንግበው የሚታገሉ አካላት ወደ ሀገራዊ ምክክሩ መድረኮች እንዲመጡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ፡፡ ኮሚሽኑ ለሚሳተፉ ታጣቂዎች ጥበቃ እንደሚደረግላቸውም ገልጿል።

የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ሥላሴ፤ ግጭት ሕይወትና ንብረትን ያጠፋል እንጂ ችግርን አይፈታም ሲሉ ገልጸው፤ “ታሪካዊ አጋጣሚ” በሆነው ሀገራዊ ምክክር በመሳተፍ ሐሳብን በማቅረብ መግባባት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በዚህም ትጥቅ አንግበው እየታገሉ ያሉ አካላት ወደ ምክክሩ እንዲመጡ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን መጥቀሳቸውን ፋና ዘግቧል።

ኮሚሽነሯ አሁንም ታጣቂዎቹ ወደ ምክክሩ እንዲመጡ በመጠየቅ ሲመጡም ጥበቃ እንደሚደረግላቸው አረጋግጠዋል፡፡

ኮሚሽኑ የሚያመቻቻቸው መድረኮችም ማንኛውም ሰው በነጻነት የሚሳተፍባቸው መሆናቸውን አስረድተው፤ ትጥቅ አንግበው የሚታገሉ አካላት ወደ ሀገራዊ ምክክር መድረኩ እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስን ጨምሮ ሌሎች የሲቪክ ድርጅቶች የኮሚሽኑን ምስረታ ሂደት እና አሳታፊነቱ ላይ ቅሬታ ሲያሰሙ ቆይተዋል። በዚህም የተነሳ በሀገራዊ ምክክሩ ከመሳተፍ እራሳቸውን አግልለዋል። 

የኦፌኮ ስራ አስፈጻሚ ኪሚቴ አባል የሆኑት ሱልጣን ቃሲም በቅርቡ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ ፓርቲያቸው ከመጀመሪያውም አንስቶ ሀገራዊ ምክክር እንዲደረግና ፖላቲካዊ መፍትሄ እንድሰፍን ጥሪ ሲያቀርብ እንደነበር ገልጸው ነገር ግን የኮሚሽኑ ምስራታ ሂደት እና እያከናወነው ያለው ስራ ላይ ቅሬታ እንዳላቸው አስረድተዋል።

ሱልጣን ኮሚሽኑ ከምስረታው ጀምሮ ሁሉን አካታች እንዲሆን፣ መሰረታዊ የሀገሪቱን ችግሮች መፍታት እንዲችል ለፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ፕሮፖሳል ማቅረባቸውን ገልጸው የፍትህ ሚንስቴር ሃሳባቸውን ሳይቀበል የራሱን ብቻ ተግባራዊ አድርጓል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ኮሚሽነሮቹ የተመረጡበት ሂደትም ግልጽነትና አካታችነት የለውም ያሉት ሱልጣን በዚህም የተነሳ ኮሚሽኑ በትጥቅ ትግል ላይ ላሉትም ሆነ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ከአድሎነት ነጻ ሆኖ፤ በግልጸነት እና በገለልተኛነት ይሰራል የሚል እምነት ስለሌለን ከመሳተፍ እራሳችንን አግለናል ሲሉ ገልጸዋል። አስ

Exit mobile version