ፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: አሜሪካ በኢትዮጵያ ጊዜያዊ ሀገር አቀፍ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠየቀች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8/2016 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ትላንት ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም የሀገራቸውን ዋነኛ ፖሊስ ባመላከቱበት ጋዜጣዊ መግለጫቸው በሀገሪቱ ወቅታዊ የደህንነት ሁኔታ፣ በሀገራዊ ምክክሩ እና በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ የሀገራቸውን አቋም አንጸባርቀዋል።

በጋዜጣዊ መግለጫቸው አምባሳደሩ በኢትዮጵያ መሳሪያ አንግበው የሚፋለሙ ሀይሎች ማናቸውም በአቋራጭ በምንም መልኩ አሸናፊ መሆን አይችሉም ሲሉ ገልጸዋል።

ድል እቀዳጃለሁ በሚል ግጭቶቹን ማስቀጠል ህዝቡን ከማሰቃየት እና ተጎጂ ከማድረግ ያለፈ የሚያመጣው ውጤት አይኖርም ሲሉ ጠቁመዋል።

ዜጎች የሚጠቀሙባቸውን መሰረተ ልማቶችን ማውደም እንዲቆም እና ያለገደብ የሰብአዊ እርዳታ እንዲዳረስ በአጽንኦት የጠየቁት አምባሳደሩ ይህም እንዲሆን መቅደም ያለበት በመላ ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ሀገር አቀፍ የተኩስ አቁም ሲደረግ ነው ሲሉ አመላክተዋል።

አምባሳደሩ “አሜሪካ ግቢ” በመባል በሚጠራው አከባቢ በሚገኘው የየመን ማህበረሰብ ትምህርት ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን መሳሪያ ባነገቡ አካላት ያለምንም ፍርድ እየተገደሉ መሆኑን፣ የዘፈቀደ ጅምላ እስር እንደሚፈጸም፣ ሰዎች በተለያዩ ቦታዎች እንደሚታገቱ፣ በግጭት ጋር የተያያዘ ጾታዊ ጥቃት እንደሚፈጸም የሚያመለክቱ ሪፖርቶችን መስማት ያስጨንቃል ሲሉ ገልጸዋል።

እነዚህ በደሎች እና ግፎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ባፋጣኝ፣ ትኩረት ተሰጥቷቸው፣ ተጠያቂነትን ባሰፈነ መልኩ፣ እውነተኛ በሆነ ግልጽነት ባለው የሽግግር ፍትህ ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።

በኦሮምያ የሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በዳሬሰላም ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያሳያችሁትን ጥረት ማቆም የለባችሁም ሲሉ የገለጹት አምባሳደሩ ይህ አካሄዳችሁ ከፍተኛ ድጋፍ በህብረተሰቡ ዘንድ እንዳስገኘላቸው በመጠቆም ሰላማዊ መንገዱ ውጤትእንዲያመጣ ጥረታቸውን ማስቀጠል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱት “የፋኖ ታጣቂዎች” በሰላማዊ ውይይት አንሳተፍም ማለታችሁ እሚፈይድላችሁ ነገር አለመኖሩን ልታውቁ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

አምባሳደሩ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ለሀገሪቱ መንግስት ባስተላለፉት መልዕክት ሀገሪቱ በጦር ሜዳ ከምታገኛቸው ውጤቶች ይልቅ በሰላማዊ ውይይት የምታገኘው ውጤት ይበዛል ሲሉ ገልጸው የሀገሪቱ ውስብስብ የፖለቲካ ሁኔታ የጸጥታ ሁኔታ ላይ ትኩረት ባደረገ መልኩ የሚፈታ አይደለም ብለዋል። ሊፈቱ የሚገቡ ችግሮችን መንግስትን የሚተቹ ፖለቲከኞችን በማሰር መፍታት አይቻልም ሲሉ ጠቁመዋል። ወነኛ የፖለቲካ ተዋናያንን በመፍታት ወደ ፖለቲካ ውይይት መግባት ይገባል ሲሉ አመላክተዋል።

ውይይት ማድረጊያው ግዜ አሁን ነው ሲሉ አሳስበዋል

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button