ዜናማህበራዊ ጉዳይ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በኦሮሚያ ክልል የመንግሥትና የታጣቁ ቡድኖች በሲቪል ሰዎች ላይ “እጅግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት” መፈጸማቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16/2016 ዓ/ም፦ በኦሮሚያ ክልል ባላፉት ሁለት አመታት የመንግሥት እና የታጣቁ ቡድኖች በሲቪል ሰዎች ላይ ባደረሱት እጅግ በርካታ ከሕግ ውጪ ጥቃቶች “እጅግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት” (grave violation of human rights) ፈጽመዋል ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ( ኢሰመኮ) አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል ከመስከረም 1 ቀን 2014 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ባሉት ሁለት ዓመታት  ከሕግ/ከፍርድ ውጪ የሆኑ እና በሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎችን በተመለከተ ያዘጋጀውን ባለ 11 ገጽ ሪፖርት ትላንት የካቲት 15 / 2016 ይፋ አድርጓል። 

ኮሚሽኑ ሪፖርቱ በክልሉ ቄለም ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉድሩ ወለጋ፣ ጉጂ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ አርሲ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ሰሜን ሸዋ እና ምሥራቅ ሸዋ ዞኖች ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጿል።  

በአካባቢዎቹ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) እና በኢ-መደበኛ የአማራ ታጣቂዎች መካከል በመካሄድ ላይ በሚገኘው ግጭት በርካታ ሲቪል ሰዎች ከሕግ ውጪ መገደላቸውን፣ ለከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት መዳረጋቸውን፣ መታገታቸውን እና ዘረፋ የተፈጸመባቸው መሆኑን አሰመኮ አስታውቋል። 

ኮሚሽኑ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በሲቪል ሰዎች ላይ ለሚደርስ የመብቶች ጥሰት እንደ ዋነኛ ምክንያት የገለጸው በመንግሥት የጸጥታ አካላት በኩል “ለታጣቂ ቡድኖች መረጃ እና ሎጂስቲክስ ታቀርባላችሁ፣ የቡድኑ አባል ናችሁ’’ በሚል ምክንያት ነው ብሏል።

በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ’’) በኩልም “ለመንግሥት መረጃ ትሰጣላችሁ፣ የቤተሰብ አባላችሁ በመንግሥት ጸጥታ ኃይል ውስጥ እያገለገለ ነው ወይም ከእኛ ጋር በመሆን አልታገላችሁም’’ በሚል፣ ምክንያት ሲቪል ሰዎችን ማጥቃት፣ ማንገላታት፣ ማገት እና ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍሉ የማድረግ ተግባር የሚከናወን መሆኑን ሪፖርቱ አመላክቷል። 

በተመሳሳይ በኢ-መደበኛ የአማራ ታጣቂዎች ከአማራ ክልል ጋር በሚዋሰኑ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ነዋሪዎችን  “በኦነግ ሸኔነት” በመፈረጅ እና የክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የመሬት ይገባኛል ጥያቄዎችን በማንሳት በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ ዘረፋ እና ማፈናቀል እንደሚፈጸም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በክልሉ በመንግስት እና በታጠቁ ኃይሎች በሲቭሎች ላይ ባዳረሱት ጥቃት ከ 90 በላይ ንጹሃን ዜጎች መሞታቸውን አዲስ ስታንዳርድ ከሪፖርቱ ተረድቷል። 

ሪፖርቱ “እነዚህ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ ግጭቶቹ በተከሰቱባቸው አካባቢዎች ላይ ሆን ተብሎ እና በተስፋፋ ሁኔታ በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸሙ” መሆናቸውን ገልጾ  ይህም “እጅግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት” (grave violation of human rights) ነው ሲል ደምድሟል። 

ኮሚሽኑ በግጭቱ ተሳታፊ አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም በማድረግ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ በቁርጠኝነት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርቧል። 

መንግሥት ኢሰመኮ የፌደራል መንግሥቱ የሰብዓዊ መብቶች እና የሰብዓዊነት ሕጎች ጥሰት የፈጸሙ እና ያስፈጸሙ ኃላፊዎች ላይ የወንጀል ምርመራ እና የክስ ሂደት እንዲጀመር ጥሪ አቅርቧል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button