ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ “በኦሮምያ ባለስልጣናት የተደራጀ ህቡዕ ኮሚቴ ከፍተኛ ወንጀሎች እንዲፈጸሙ ትዕዛዝ ይሰጥ ነበር” – የሮይተርስ የምርመራ ሪፖርት

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15/2016 ዓ.ም፡- ሮይተርስ የዜና ወኪል አካሄድኩት ባለው ለወራት የዘለቀ ምርመራ በኦሮምያ በክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት የተቋቋመ እና በህቡዕ የተደራጀ ኮሚቴ፣ የጸጥታ ሀይሎች ከፍተኛ ወንጀሎችን እንዲፈጸሙ፣ ተቃማሚዎችን እንዲያጠፉ ትዕዛዝ ይሰጥ ነበር ሲል አስታወቀ።

የህቡዕ አደረጃጀት አለው የተባለው ኮሚቴው ስያሜው “ኮሬ ነጌኛ” ወይንም የጸጥታ ኮሚቴ መሆኑን እና ዶ/ር አብይ አህመድ ጠ/ሚኒስትር ሁነው በተሾሙ ወራት ውስጥ የተቋቋመ መሆኑን የዜና አውታሩ በሪፖርቱ ጠቁሟል።

የተቋቋመበትም ዋነኛ አላማ በክልሉ ከሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ሀይል ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር በተገናኘ በኦሮምያ ክልል የተነሳውን ተቃውሞ  ለመቆጣጠር መሆኑን አመላክቷል።

ኮሚቴው የሚመራው በኦሮምያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ መሆኑን እና በአባልነት የክልሉ ከፍተኛ የጸጥታ እና የፖለቲካ ባለስልጣናት እንደሚገኙበት ጠቁሟል።

የዜና አውታሩ የምርመራ ሪፖርቱን ለማጠናቀር 30 የቀድሞ እና በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ ያሉ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ቃለመጠየቅ ማካሄዱን፣ ጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ዶክመንቶችን መጠቀሙን አስታውቋል።

በኮሚቴው በተላለፈ ትእዛዝ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ የተፈጸሙ ግድያዎች፣ “የጸጥታ ስጋቶች” ናቸው በሚል የተፈጸሙ ጅምላ እስሮች በዜና አውታሩ ሪፖርት ተካተዋል። በ2014 ዓ.ም በከረዩ አባገዳዎች ላይ የተፈጸመው ግድያ ጋር በተያያዘ ሮይተርስ በምርመራ ማለትም ከሚስጥራዊ ሰነዶች እና ቃለምምልሶች አገኘሁት ባለው መረጃ ከህቡዕ አደረጃጃቱ በተላለፈ ትእዛዝ እንዲገደሉ ተደርገዋል ብሏል።

ኮሚቴው በፍትህ ስርአቱ በስፋት ጣልቃ በመግባት ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ እና የፍርድ ሂደቱን ባልተከተለ መልኩ ሰዎች እንዲያዙ ያለፍርድ ሂደት በእስር እንዲቆዩ ተደርገዋል ብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በእስር ላይ የሚገኙትም ተገርፈዋል፣ እንዲሰቃዩ ተደርገዋል ያለው ሮይተርስ ጣልቃ ለመግባት እና ለመገዳደር የሞከሩ ዳኞች እና ጠበቆች ማስፈራራት ደርሶባቸዋል ሲል ገልጿል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የኮሚቴውን መኖር አረጋግጠልኛል ያለው ሮይተርስ ከኮሚቴው ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ ከህግ አግባብ ውጭ ግድያዎች፣ የዘፈቀደ ጅምላ እስሮች እና ግርፋቶች በኮሚሽኑ ማጠናቀሩን ጠቁሟል።

በጉዳዩ ዙሪያ የኦሮምያ ክልል መንግስት ምላሽ እንዲሰጥበት ሮይተርስ ሙከራ ማድረጉን እና ምልሻ እንዳልተሰጠው በሪፖርቱ አካቷል። የጥሰቶቹን ሂደት በማሳያነት መመልከት በራሱ ግልጽ ማስረጃ ቢሆንም፣ ተፈጽሟል የተባለውን እያንዳንዱ የመብት ጥሰትን ሮይተር በገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻልኩም ሲል በሪፖርቱ አመላክቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button