ዜናፖለቲካ

ዜና፡ ወደ አዋሽ አራባ ወታደራዊ ካምፕ ተወሰደው በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ሲፒጄ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 25/ 2015 .ም፡ ዓለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ (ሲፒጄ) በኢትዮጵያ በነሃሴ መጨረሻ እና በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ የታሰሩ ሶስት ጋዜጠኞችን መንግሰት በአስቸኳይ እንዲፈታ ጠየቀ፡፡

ሲፒጄ የ”የኛ ቲቪ” እና “የምኒሊክ ቴሌቪዥን” የኦንላይን ሚዲያ አቅራቢ እና ፕሮግራም አዘጋጅ ቴዎድሮስ ዘርፉ ነሃሴ 20፣ 2015፣ የፖለቲካ ተንታኝና የየኛ ፎረም ፕሮግራም ተባባሪ አቅራቢ ንጉሴ ብርሃኑ ነሃሴ 24 እና የትርታ ኤፍ ኤም የፕሮግራም ዳይሬክተር የሆነው ጋዜጠኛ የኋላሸት ዘሪሁን ጳጉሜ 6፣ 2016 በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጧል፡፡

ሶስቱም ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ወደ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ መወሰዳቸውን የገለፀው ሲፒጄ ነገር ግን በኋላ ላይ ወደ አዋሽ አርባ ወታደራዊ ማቆያ ማዕከል መዘዋወራቸውን ትላንት መስከረም 24፣ 2016 መግለጫ መግለጫ አስታውቋል፡፡

በአማራ ክልል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በኢትዮጵያ የሚፈፀሙት የጋዜጠኞችን እስር እንዳሳሰበው የገለፀው ድርጅቱ ጋዜጠኞቹ ፍርድ ቤት ቀርበው በወንጀል መከሰሳቸውን እንደማያውቁ አክሎ ገልጧል፡፡

የድርጅቱ ከሰሃራ በታች ተወካይ ሙቶኪ ሙሞ “ጋዜጠኞቹን ግልፅ ባልሆነ የፍርድ ሂደት በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ማሰር  የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን የደረሰበትን አሳሳቢ ደረጃ የሚያሳይ ነው” ሲሉ ገልፀው፣ “የመንግስት ባለስልጣናቱ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ዘርፉ፣ የኋላሸት ዘሪሁን፣ ንጉሴ ብርሃኑ እንዲሁም ሌሎች በስራቸው የታሰሩ የፕሬስ አባላት ሊፈቱ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።

ሲፒጄ ተጨማሪ መረጃን ለማግኘት ለፌዴራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ጄይላን አብዲ እና ለፍትህ ሚኒስቴር ጽ/ቤት እና ለመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቃል አቀባይ ለ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ለላከው መልዕክት ምላሽ አለማግኘቱን ገልጧል፡፡አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button