ፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል በህወሓት ላይ ያቀረበውን ክስ አስተባበለ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 29/2016 ዓ.ም፡- በመሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሔሜቲ) የሚመራው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል የህወሓት ሀይሎች በአልቡርሃን የሚመራው የሱዳን መደበኛ ጦር ጋር ተሰልፈው እየወጉኝ ነው ሲል ባወጣው መግለጫ ወንጅሏል።

በአልቡርሃን የሚመራው የሱዳን መደበኛ ጦር የውጭ ሀገር ተወላጅ ተዋጊዎችን በመመልመል እየተዋጋ ስለመሆኑ በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የተረጋገጠ ነው ያለው የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ መግለጫ የሌላ ሀገር ተወላጅ ሁነው ከሚወጉኝ መካከል ህወሓት ይገኝበታል ሲል አስታውቋል። በቂ ማስረጃም አለኝ ብሏል።

በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ ያወጣው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር “የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ውንጀላ መሰረት የለሽ ነው” ሲል አስተባብሏል።

ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ በሱዳን ሰራዊት ላይ የሚያካሂደው ዘመቻ አለም አቀፍ ድጋፍ ለማግኘት በማለም ብቻ የተቀነባበረ ወንጀል ነው ሲል ገልጿል።

“ከሁሉም በላይ ህወሓት ፖለቲካ ፓርቲ እንጂ የታጠቀ ሀይል የለውም” ያለው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መግለጫ “የሚያዘው ሚሊሻም ይሁን ማንኛውም የታጠቀ አካል የለውም” ብሏል።

ሌላኛው መግለጫው ያነሳው ነጥብ ደግሞ የትግራይ ህዝብ የቆየ ወንድማዊ ግንኙነት ከሱዳን ህዝብ ጋር ያለው መሆኑን ሲሆን ዘመናትን በፈተና ተሻግሮ የጸና ነው ሲል አመላክቷል።

በትግራይ በተካሄደው ጦርነት ሳቢያ የምዕራብ ትግራይ ነዋሪዎች በተፈናቀሉበት ወቅት ከለላ እናገኛለን በማለት የተሰደዱት ወደ ሱዳን ነው ያለው መግለጫው የሱዳን ህዝብ እና መንግስት በችግር ላይ እያሉም ቢሆን የሚቻላቸውን እገዛ አድርገዋል ሲል አወድሷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በነዚህ ምክንያቶች በሱዳን በመካሄድ ላይ ባለው የእርስ በርስ ግጭት ጣልጋ መግባት አንፈልግም ያለው የጊዜያዊ አስተዳደሩ መግለጫ በትግራይ ተወላጆች ዘንድ እንደ ሁለተኛ ቤታቸው ተደርጋ በምትቆጠረው ሱዳን ላይ ጣልቃ በመግባት ሁኔታዎችን ማባባስ አንፈልግም ሲል ጠቁሟል።

የውጭ ጣልቃ ገብነት የሚያደርሰውን ውድመት የተሞላበት ውጤት ከትግራይ ህዝብ በተሻለ የሚያውቀው የለም ሲል የጠቆመው መግለጫው በውጭ ሀይሎች ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ ጣልቃ ገብነት ሳቢያ የረደሰበትን ስቃይ ጠንቅቆ ያውቀዋል ብሏል።

ትግራይ በሱዳን እርስ በርስ ጦርነት ላይ ጣልቃ ለመገባት የሚያስችላት ምንም አይነት ምክንያት የላትም ብሏል።

የሱዳን ተፋላሚ ሀይሎች ግጭቱን የሚያባብስ ሁኔታዎችን ከመፍጠር እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርቧል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button