ህግ እና ፍትህዜና

ዜና: በምዕራብ ወለጋ ቤጊ እና ቆንዳላ ወረዳዎች ሶስት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ፤ የሟች ቤተሰቦች “የመንግስት ሃይሎችን” ተጠያቂ አድርገዋል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18/2017ዓ/መ:- በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ቤጊ እና ቆንዳላ ወረዳዎች ሶስት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው የተገለጸ ሲሆን ነዋሪዎች እና የሟች ቤተሰቦች ግድያው የተፈጸመው “በመንግስት ታጣቂዎች ነው”ሲሉ ገልጸዋል።

በግድያው ህይወታቸውን ያለፈው አቢብ ብርሃኑ ወንድም የሆኑት ቃሲም ብርሃኑ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት የ22 አመት ወንድማቸው መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም. “በመንግስት ታጣቂዎች በጥይት ተመቶ መገደሉን” ተናግረዋል።

በወቅቱ ወንድማቸው አቢብ በቤጊ ከተማ ከገበያ ወደ ቆንዳላ ወረዳ ሸጋ ቀበሌ እየተመለሰ እንደነበረ አስረድተዋል።

አቶ ቃሲም አክለውም “የመንግስት ሃይሎች አቢብን በቤጊ ከተማ ካንቶ አስቁመው ተኩሰውበታል” ሲሉ የገለጹ ሲሆን፤ በወቅቱ ቤጊ ወደሚገኝ ሆስፒታል በፍጥነት ቢወሰድም ሆስፒታሉ እንደደረሰ ወድያውኑ በ“አሳዛኝ” ሁኔታ ህይወቱ እንዳለፈ ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም አዲስ ስታንዳርድ በሐምሌ 2016 ዓ.ም. ባወጣው ዘገባ በቤጊ ወረዳ ካርማ ጉንፊ ቀበሌ ሁለት ነዋሪዎች “በመንግስት ሃይሎች” መገደላቸውን መዘገቡ ይታወሳል።

በወቅቱ ዘገባው በዝርዝር እንደገለጸው ሐምሌ 8/ 2016 ዓ.ም. የመንግስት ሃይሎች ረመዳን ጂባን እና ቶፊቅ ዳማራ የተባሉ ግለሰቦችን በመያዝ ላሎ ተብሎ ወደሚጠራው የጦር ካምፕ ከወሰዷቸው በኋላ ከቀኑ 9፡00 ሰአት አካባቢ አስከሬናቸው በቤጊ ቆንዳላ መንገድ ላይ ተገኝቷል።

በምዕራብ ኦሮሚያ በመንግስት ሃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል የሚደረገው ግጭት የሰው ህይወት መቅጠፉን ቀጥሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በቤጊ ወረዳ ግድያው በተፈጸመ በተመሳሳይ ቀን በቆንዳላ ወረዳ ሌላ “አሳዛኝ” ክስተት ተፈጥሮ የሁለት ንፁሃን ዜጎች ህይወት አልፏል።

በግድያው ህይወታቸውን ያለፈው ረኪሳ ሀሩን ወንድም የሆኑት ኢዶሳ ሀሩን ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት የ28 ዓመት ወንድማቸው ራኪሳ ከሌሎች 36 ዓመት ከሆናቸው ሁለት ግለሰቦች ማለትም ዳሲሳ ዋቶ እና ረመዳን አሳን ጋራ በ”መንግስት ታጣቂዎች” በቆንዳላ ወረዳ መያዛቸውን ጠቁመዋል።

አክለውም ግለሰቦቹ “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን በመደገፍ” እና “በቆንዳላ ከተማ ገበያውን በማደናቀፍ” በሚል መከሰሳቸውን ተናግረዋል።

የሟች ራኪሳ ሀሩን ወንድም የሆኑት ኢዶሳ  መስከረም 12 ቀን 2016ዓ.ም. ጠዋት ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ቤታቸው ደርሰው ራኪሳን “ከኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ጋር ግንኙነት አለህ” በማለት ወደ ቆንዳላ ወታደራዊ ካምፕ እንደወሰዱት አስታውሰዋል።

ለሶስት ቀናት ያህል ምግብ እና ቡና በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ለነበረው ለራኪሳ ሲያመላልሱለት እንደነበር የገለጹት ኢዶሳ ነገር ግን መስከረም 15/2016 ዓ.ም. ጠዋት ላይ የራኪሳን እና የረመዳንን አስከሬኖች ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የራኪሳ አስከሬን ወደ ሸጋ ዲንቃ ቀበሌ በሚወስደው መንገድ ላይ ጀርባና ጭንቅላቱ ላይ በጥይት ተመትቶ መገኘቱን እንዲሁም የረመዳን አስከሬን በሸጋ ዲንቃ ቀበሌ ኦፋፋ ወንዝ ውስጥ ደረቱ ላይ ተመትቶ መገኘቱን ኢዶሳ አስረድተዋል።

እንደ መረጃ ምንጩ ሁለቱም ሰዎች እያንዳንዳቸው የሁለት ልጆች አባት ነበሩ።

በቅርቡ የቤጊ እና የቆንዳላ ወረዳ ነዋሪዎች ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ በአከባቢያቸው በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልፀዋል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button