ዜናፖለቲካ

ዜና፡ በአማራ ክልል ከተሞች በተካሄደ ከባድ ግጭት "የጸጥታ አባላትን" ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8/2016 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል የማዕከላዊ ጎንደር ዞን መቀመጫ በሆነችው ጎንደር እና በተለያዩ አካባቢዎች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ሰሞኑን እየተካሄደ ባለ ግጭት “የጸጥታ አባላትን” ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።  

በጎንደር ከተማ ሰሞኑን ግጭት እየተካሄድ መሆኑን ለአዲስ ስታንዳርድ የተናገሩ የከተማዋ ነዋሪ፤ ትናንት ከጠዋቱ 12 ሰዓት አከባቢ ጀምሮ እስከ ምሽቱ 11ሰዓት ድረስ በተለያዩ የከተማዋ ስፍራዎች “ከባድ ውጊያ” ሲደረግ መዋሉን ተናግረዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት ነዋሪው፤ ቀበሌ 18፣ ሸዋ ዳቦ ከሚባል አካባቢ እስከ ሐምሌ 5 የሚባለው አከባቢ ድረስ “ከባድ የተኩስ እሩምታ” ነበር ብለዋል።

ግጭቱ የተቀሰቀሰው የ”ፋኖ ሃይሎች በከተማዋ የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊትን ምሽጎች ለመስበር ባደረጉት ሙከራ ነው”  ሲሉም አክለው ገልጸዋል።

“እኛ ባለንበት አከባቢ በመጀመሪያው ምሽግ ብቻ 6 የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተገድለዋል” ያሉት ነዋሪው አክለውም ከፋኖ ታጣቂዎች በኩል ተመትተው የቆሰሉ እንዳሉ መስማታቸውን ገልጸዋል።

በትናንትናው ዕለት በከተማዋ በአምስት አቅጣጫዎች ውጊያዎች ሲደረጉ መዋላቸውን ሌላ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሌላ ነዋሪ ተናግረዋል።

አዲስ አለም አከባቢ፣ በተለምዶ “ገንፎ ቁጭ” አሁን አየር ጤና በሚባለው አከባቢ ገብርኤል ቤተክርስትያን አቅራቢያ፣ አማኑኤል ቤተክርስያን አከባቢ፣ ቀበሌ 18 እና ሐምሌ 5 የተሰኙ ቦታዎች ግጭቶች ሲካሄዱባቸው ከዋሉ ስፍራዎች መካከል እንደሚገኙበት ነዋሪው ጠቁመዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ነዋሪው አክለውም በትናንትናው ዕለት ግጭት ከተኩስ እሩምታው በተጨማሪ ከባባድ መሣሪያዎች ሲተኮሱ እንደነበር ገልጸው፤ በዚህም በቀበሌ 18 ብቻ እስከአሁን በትንሹ 2 ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸውን እንዲሁም ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መቁሰላቸውን ተናግረዋል። 

በተጨማሪም ከከተማዋ ወጣ ብላ በምትገኘው ፈንጠር አከባቢ በተመሳሳይ ከባድ መሣሪያ ሲተኮስ እንደዋለ ገልጸዋል።

ሌላ ነዋሪነታቸው በጎንደር የሆኑ እና ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ግለሰብ በበኩላቸው የትናንትናው ግጭት ከበድ ያለ እንደነበር ሁኔታውን ለአዲስ ስታንዳርድ በሰጡት ቃል አስረድተዋል።

“ጎንደር ስትናጥ ነበር የዋለችው።” ያሉት ነዋሪ አክለውም “ከከባድ መሣሪያ ተኩሱ በተጨማሪ ቅርብ ለቅርብ ሲካሄድ በነበረው ውጊያ በተባራሪ ጥይት የተመቱ ሰዎች መኖራቸውን” ጠቁመዋል።

ነዋሪው አክለውም ከሰሞኑ በጎንደር ከተማ ዙርያ ሲደረግ በሰነበተው ውጊያዎች በተለይም “አይምባ” በተባለው አከባቢ ከባድ ውጊያ እንደነበረ ጠቁመዋል። በዚህም አከባቢው “ከ3 ቀናት በፊት በፋኖ ሃይሎች ቁጥጥር ስር ውለዋል” ብለዋል። 

በተመሳሳይ በማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት ትናንት መስከረም 7/2017ዓ.ም.በነበረው በከባድ መሣሪያ የታገዘ ተኩስ ሁለት ንጹሐን የአቋቋም ደቀ መዛሙርት መሞታቸውን እንዲሁም ሦስት የአቋቋምና ሁለት የቅኔ ደቀ መዛሙርት በጽኑዕ መቁሰላቸውን ተዋህዶ ሚዲያ ማዕከል ዘግቧል

ከተገደሉት ተማሪዎች ውስጥ አንዱ ቤዛዊት ማርያም ፣ አንዱ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን የአቋቋም ትምህርት በመማር ላይ የሚገኙ ሲሆን በጽኑዕ የቆሰሉት ተማሪዎች ሁለቱ አማኑኤል ቤተክርስቲያን የአቋቋም ትምህርት ሁለቱ በደብረ መዊዕ ርዕሰ አድባራት አበራ ጊዮርጊስ የቅኔ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ መሆናቸው ተጠቁሟል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ዛሬ ባወጣው አጭር መግለጫ፤ ትናንት መስከረም 07/2017 ዓ.ም የፀጥታ ችግር መፈጠሩን ጠቅሶ፣ በዚህም ምክንያት ተቋርጦ የነበረዉ የትራንስፖርት አገልገሎት ዛሬ “በተሟላ ሁኔታ መጀመሩን” አመላክቷል።

ይሁን እንጂ አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደገለጹት በአሁኑ ሰዓት በከተማዋ ትራንስፖርትን ጨምሮ የግል እና የመንግስት ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ብለዋል። 

በተጨማሪም የሰሜን ጎንደር ዞን መቀመጫ በሆነችው በደባርቅ እንዲሁም በዳባት እና በአምባ ጊዮርጊስ ከተሞች ውጊያው ሲደረግ መሰንበቱንና በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

በደባርቅ ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያ በደባርቅ በነበረ ከፍተኛ ውጊያ ምክንያት ሰኞ ዕለት፣ መስከረም 6 2017 ዓ.ም. ብቻ ከ20 በላይ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ገልጸዋል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button