ህግ እና ፍትህዜና

ዜና፡ በኢትዮጵያ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተባብሰው መቀጣላቸውን ኢሰመኮ ገለጸ፤ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16/ 2017 ዓ/ም፦ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኢትዮጵያ በተለይም በግጭት ዐውድ ውስጥ ያሉ አካባቢዎች የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አሳሳቢ ሆነው መቀጠላቸውን አስታወቀ። 

ኮሚሽኑ ከሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. እስከ መስከረም ወር 2017 ዓ.ም. መጀመሪያ ድረስ ያካተተ የሩብ ዓመት ሪፖርት ትናንት መስከረም 15 ቀን 2017 ዓ/ም ይፋ ያደረገ አድርጓል። 

ኢሰመኮ በሪፖርቱ፤ በግጭት ዐውድ ውስጥ ባሉ አካባቢዎች ከሕግ ውጭ የሚፈጸም ግድያ፣ በግጭት ዐውድና አካባቢ የሚደርስ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ፣ የዘፈቀደ፣ የጅምላና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት፣ አስገድዶ መሰወር፣ እገታ፣ በመዘዋወር መብትና በመጓጓዣ መንገዶች ላይ የሚፈጸም ሕገ-ወጥ ገደብ እና የሀገር ውስጥ መፈናቀል አሳሳቡ ደረጃ ደርሰዋል ብሏል።

ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ አመያ ወረዳ ከኖ ቁሊጢ፣ አብየ ኮንሲ እና ቆታ ቀበሌዎች ልዩ ቦታው ቆታ (አርብ ገበያ) ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በማለት የሚጠራው ቡድን (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ታጣቂዎች መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በፈጸሙት ጥቃት የሰው ሕይወት ማለፉን ገልጿል። 

ጥቃቱን ተከትሎ ሁኔታውን ለማረጋጋት የኦሮሚያ ጸረ-ሽምቅ ውጊያ ፖሊስ አባላት በቦታው ሲደርሱ በቦታው ከነበሩ የአማራ ታጣቂዎች ጋር በተደረገ የጥይት ተኩስ በግጭቱ ውስጥ ምንም ተሳትፎ ያልነበራቸው 3 የአካባቢው ነዋሪዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ ገልጿል። ከዚህ ግጭት ጋር ተያይዞ በተጠቀሱት ቀበሌዎች ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ተፈናቅለዋል ብሏል።  

በክልሉ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን፣ አቤ ዶንጎሮ ወረዳ፣ ጨሩ ቀበሌ በአካባቢው እንደሚንቀሳቀስ የተገለጸ የአማራ ታጣቂዎች ቡድን አባላት በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በከፈቱት ተኩስ 22 ሰዎች ሲገደሉ በ4 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሷል ሲል ሪፖርቱ ገልጿል። በተጨማሪም 540 መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን እና በግምት 800 አካባቢ ከብቶች (በጎች እና ፍየሎችን ጨምሮ) በታጣቂ ቡድኑ መዘረፋቸውም ተመላክቷል።

በተመሳሳይ በአርሲ ዞን፣ አሰኮ ወረዳ፣ ጠለፋ ጨፋ ቀበሌ  ነሐሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትታጣቂዎች ወደ ቀበሌው ገብተው የቀበሌው አስተዳደር ሲቪል ሠራተኞች እና ከመንግሥት ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠቆሙ ነዋሪዎችን ለይተው በወሰዱት ጥቃት ሶስት ሰዎችን ገድለው፣ አንድ ሰው ላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የበርካታ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶችንም አቃጥለዋል ያለው ሪፖርቱ ብዛታቸው ያልታወቀ ሰዎች ጥቃቱን በመሸሽ አካባቢውን ለቀው ወደ አሰኮ ከተማ አካባቢ ሠፍረው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል ሲል ገልጿል። 

በአማራ ክልልም እንዲህ ያሉ ተመሳሳይ ጥቃቶች በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት እንደሚፈጸሙ ኮሚሽኑ ገልጿል።

ግንቦት ወር በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ የኤፍራታና ግድም ወረዳ አስተዳዳሪ እና የቀወት ወረዳ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በ“ፋኖ” አባላት በመኖሪያ ቤታቸው ተገድለዋል ብሏል። 

ሰኔ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ወደ ሰሜን ሜጫ ወረዳ ወተት አባይ ቀበሌ አቅጣጫ በመጓዝ ላይ እያሉ መከኒ ዋርካ ቀበሌ አልቃ በተባለ ቦታ ላይ “በ“ፋኖ” አባላት ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በበቀል ስሜት በጉዟቸው ላይ ያገኟቸውን 10 አርሶ አደሮችን በጥይት የገደሉ ሲሆን ሌሎች 2 አርሶ አደሮችን ደግሞ ያቆሰሉ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል” ሲል ሪፖርቱ አትቷል። 

ከአንድ ቀ በኋላ ሰኔ 9 ቀን ምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ጅጋ ከተማ አስተዳደር፣ “ጎህ” በተባለ ካፌና ሬስቶራንት ውስጥ የነበሩ ሰዎችን ጨምሮ ቢያንስ 16 ሰዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጭ መገደላቸውን የሟች ቤተሰቦች፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና የመንግሥት አስተዳደር አካላት መግለጻቸውን ሪፖርቱ አክሏል።

መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም. ሰሜን ጎንደር ዞን፣ ደባርቅ ከተማ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በ“ፋኖ” አባላት መካከል ከተካሄደው የትጥቅ ግጭት ጋር በተያያዘ ዒላማቸውን ባልጠበቁ ተኩሶች እና በተባራሪ ጥይቶች ቢያንስ 20 ሲቪል ሰዎች እንደተገደሉ ኢሰመኮ ገልጿል።

 9 ሰዎች ደግሞ ከቤታቸው እየተወሰዱ በመንግሥት የጸጥታ አካላት እንደተገደሉ ነዋሪዎች ተናግረዋል ተብሏል። ከእነዚህ ውስጥ ከገጠር ወደ ደባርቅ ከተማ መጥተው አልጋ ይዘው የነበሩ 5 መምህራን ይገኙበታል።

በተመሳሳይ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጋምቤላ ክልል፣ ከሕግ ውጭ ግድያ፣ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ መፈጸሙም ሪፖርቱ አስታውቋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት “ሸኔ”ን እና “ፋኖ”ን ይደግፋሉ ተበለው በቁጥጥር ስራ ከዋሉ ሰዎች መካከል ፍርድ ቤት ያልቀረቡ እንዲሁም ያልተፈቱ መኖራቸውም ተመላክቷል።

በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከተራዘሙ የትጥቅ ግጭቶች ጋር ተያይዞ በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው የሕግ ማስከበር እና የመንግሥት መዋቅር መላላት ሳቢያ የሚፈጸሙ እገታዎች አሁንም ተባብሰውና ተስፋፍተው መቀጠላቸውን ሪፖርቱ አስታውቋል።

በመጨረሻም ምክረሃሳብ ያቀረበው ኢሰመኮ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በግጭት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም በማድረግ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ በቁርጠኝነት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርቧል።

በማናቸውም የግጭት ሂደት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎች ጥሰትን ከመፈጸም እንዲቆጠቡ፤ በግጭቱ የሚፈጸሙ ጥሰቶችን በይፋ እንዲያወግዙ እና ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡም ጠይቋል።

በአማራ ክልል በቀጠለው የትጥቅ ግጭት ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች የመዘዋወር ነጻነትና መጓጓዣ ላይ የሚያደርጉትን ተገቢ ያልሆኑ ገደቦችን ጨምሮ ኅብረተሰቡን ከሚያማርሩ እና ነጻነትን ከሚገድቡ ድርጊቶች እንዲቆጠቡም ኮሚሽኑ አሳስቧል።

ኢሰመኮ መንግሥት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በመካሄድ ላይ በሚገኙት የትጥቅ ግጭቶች፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎች ጥሰት የፈጸሙ እና ያስፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ የወንጀል ምርመራ እና የክስ ሂደት እንዲጀመር አክሎ ጠይቋል።

እንዲሁም በግጭቶቹ በሰው ሕይወት፣ በአካል፣ በሥነ-ልቦና እና በንብረት ላይ ያደረሱትን ጉዳት በማጣራት ተጎጂዎች እንዲካሱ እና መልሰው እንዲቋቋሙ እንዲያደርግ፣ ሁሉም ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እንዲመቻች ጥሪ አቅርቧል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button