ማህበራዊ ጉዳይዕለታዊፍሬዜና

ዕለታዊ ዜና፡ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በካይሮ ሲካሄድ የነበረው ሶስተኛው ዙር ድርድር መጠናቀቁ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14/2016 ዓ.ም፡- በግብጽ ካይሮ ሲካሄድ የነበረው ሶስተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር መጠናቀቁ ተገለጸ። በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደርና የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን መሪ አምባሰደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) “ድርድሩ መጠነኛ መሻሻል እና መግባባት” የታየበት ነው ብለዋል።

የግድርድሩ ሂደት አሁንም እንደሚቀጥል እና አራተኛው ዙር የሶስትዮሽ ድርድር በታህሳስ ወር በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ጥቅምት 12 እና 13 ቀን 2016 ዓ.ም በግብጽ ካይሮ የተካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ለሶስተኛ ግዜ የተካሄደ ሲሆን የድርድሩ ዋነኛ ትኩረት በግድቡ ውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ እንደነበር ሚኒስቴሩ በመግለጫው አመላክቷል።

በህዳሴ ግድበ ዙሪያ ሲካሄዱ የነበሩት ድርድሮች ለሁለት አመታት ከአምስት ወራት መቋረጥ በኋላ ባሳለፍነው አመት ነሃሴ 21 እና 22 ቀን 2015 ዓ.ም በካይሮ በሶስቱ ሀገራት መካከል በተካሄደ ድርድር እንደገና መጀመሩ ይታወሳል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን በማገልገል ላይ የሚገኙት ዶ/ር ስለሺ በቀለ በካይሮው ስብሰባ ኢትዮጵያን በሚኒስቴርነት ደረጃ በመወከል በዋና ተደራዳሪነት መሳተፋቸውን ያስታወቀው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ በግብጽ በኩል የውሃ ሀብት እና የመስኖ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ሃኒ ሰዊላም፣ በሱዳን በኩል ደግሞ ተጠባባቂ የመስኖ እና ውሃ ሃብት ሚኒስትሩ ኢንጂነር ዳዌልቢት አብደልራህማን መሳተፋቸውን ጠቁሟል።

ሶስቱም ተወካዮች ድርድሩን ለማጠናቀቅ በሚያስችሉ አግባቢ ነጥቦች ላይ መወያየታቸውንም መግለጫው አመላክቷል።አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button