ቢዝነስዜና

ዜና፡ በሩብ አመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ109 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ ተገለጸ፣ በመዲናዋ 33 ቢሊየን ብር መሰብሰቡ ተጠቁሟል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 14/2016 ዓ.ም፡- በ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ109 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስቴርን ዋቢ በማድረግ ኢዜአ ዘግቧል።

የ2016 የመጀመሪያ ሩብ በጀት ዓመት የመንግሥት የሥራ አፈጻጻም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት መገምገሙን የጠቆመው ዘገባው በበጀት አመቱ በአጠቃላይ 529 ቢሊዮን ብር ግብር ለመሰብሰብ እቅድ ተቀምጦ ወደ ስራ መግባቱን የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ መናገራቸውን አስታውቋል። ከዚህም ውስጥ 110 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብሩን በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለመሰብሰብ ታቅዶ፤ 109 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብሩን በመሰብሰብ የእቅዱን 99 ነጥብ 2 በመቶ ማሳካት መቻሉን ሚኒስትሯ ተናግረዋል ብሏል።

በሌላ ዜና በአዲስ አበባ በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ33 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የኢፕድ በዘገባው አስታውቋል። በበጀት አመቱ ከ140 ቢሊዮን በላይ ብር ለመሰብሰብ መታቀዱንም ጠቁሟል።

በከተማዋ ውስጥ ከገቢ እንቅስቃሴው ጋር 32 የሚሆኑ ሴክተር ተቋማትና 11 ክፍለ ከተሞች ጋር በጋራ በመሆን ሥራው እንደሚከናወን የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊው አደም ኑሪ መናገራቸውን አስታውቋል።

በገቢ አሰባሰብ ሂደቱ ከገቢዎች ቢሮ 100 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር፣ ከሴክተር ተቋማት 26 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከክፍለ ከተሞች ሦስት ቢሊዮን ብር እንደሚጠበቅ ገልጸው፤ ብድርና ዕርዳታን ጨምሮ በድምሩ ከ140 ቢሊዮን ብር በላይ ይሰበሰባል ማለታቸውንም አካቷል።

በዲጂታል የአከፋፈል ሥርዓት ማለትም፤ በሲቢኢ ብር፣ በሞባይል ባንኪንግና ቴሌ ብር አማካኝነት ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል ማለታቸውን ያስነበበው ዘገባው ግብር ከፋዩ የታክስ ሕጎችን ማክበር እንዳለበት በመጥቀስ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ ያለ ደረሰኝ ግብይት የፈጸሙ 339 ተጠርጣሪዎች እጅ ከፍንጅ ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው እንዳለም መግለጻቸውነ አመላክቷል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button