ዜናፖለቲካ

ዜና፡ በርካታ ተፈናቃዮችና ሚሊሻዎች እየተመለሱ ባሉበት ወቅት በራያ አላማጣ ፍርሃትና የጸጥታ ስጋት ሰፍኗል

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 16/ 2016 ዓ/ም፦  የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለፉት ሶስት ቀናት ሚሊሻዎችንና የቀድሞ ፖሊስ መኮንኖችን ጨምሮ 17,000 ተፈናቃዮችን ወደ ራያ አላማጣና እና ወደ አካባቢው እንዲመለሱ አድርጓል። 

የደቡብ ትግራይ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሃፍቱ ኪሮስ ማማይጨው እና መኮኒ ከተማ ተጠልለው የነበሩ 16,868 ተፈናቃዮች ወደ አላማጣ እና በአቅራቢያ ወደሚገኙ እንደ ዋጃ እና ጥሙጋ መመለሳቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። 

እንደ አስተዳዳሪው ገለፃ፣ የተመለሱት ተፈናቃዮች በ2012 ዓ/ም የትግራይ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት በአካባቢዎቹ ይኖሩ እና ይሠሩ የነበሩ ሚሊሺያ እና የፖሊስ መኮንኖች ናቸው። ቤታቸው ከወደመባቸው ተፈናቃዮች በስተቀር የተቀሩት ወደ ቀዬአቸው የተመለሱ ሲሆን ሚሊሺያዎችና ፖሊሶች በአካባቢው በሚገኝ ትምህርት ቤት ውስጥ በጊዜያዊነት እንደሚገኙም አክለው ገልጸዋል።

“እነሱም የአካባቢውን ደህንነት ለማስጠበቅ ኃላፊነት ከተሰጣቸው መከላከያ ሠራዊት እና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመተባበር ቀስ በቀስ ወደ ቀዬአቸው ይመለሳሉ” ሲሉ አቶ  ሃፍቱ ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ በቅርቡ ወደ አማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ እና ከዋግ ኽምራ ዞን ተፈናቅለው የነበሩ ከ450 በላይ ሚሊሻዎች፣ ፖሊሶች እና አመራሮች፤ ሐምሌ 14 ቀን ወደ ኮረም ከተማ እንዲመለሱ መደረጉን ከአማራ በኩል የሆኑ ምንጭ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጧል።

ምንጩ አክሎም፤ ተፈናቃዮቹ የተመለሱት የፌዴራል መንግስት እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በደረሱበት ስምምነት መሰረት መሆኑን ገልጾ፤ “የተመለሱት የታጠቁ ሚሊሻዎች እና ፖሊሶች ምንም አይነት የስራ ኃላፊነት አይወስዱም፣ ነገር ግን ከአካባቢው ህዝብ ጋር ይቀላቀላሉ” ብለዋል።

ይሁን እንጂ ሚሊሻዎችና ፖሊሶችንን ጨምሮ የተፈናቃዮች መመለስ፤ ባለፈው ቅዳሜ ሰልፎችን ባካሄዱ የአካባቢው የአማራ ወጣቶች ተቃውሞ ገጥሞታል። ማክሰኞ ዕለት አራት የአማራ ወጣቶች “በትግራይ ታጣቂዎች” ታግተው መወሰዳቸውን ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ጉዳዩን በተመለከተ በትግራይ ክልል በኩል የአላማጣ ከተማ ከንቲባ፤ “ረብሻ በመፍጠራቸው” ምክንያት የትግራይ ሚሊሻ አባላት ተይዘው ለፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ተላልፈው መሰጠታቸውን ተናግረዋል።

ስሙ አንዳይጠቀስ የጠየቀ ነዋሪ፤ ተፈናቃዮች የመመለስ ሂደት እየተከናወነ ባለበት ወቅት ፍርሃት እና የጸጥታ ስጋት መንገሱን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጿል። “በየትኛውም አካል ቁጥጥር ስር ቢሆንም ሰዎች ፍርሃት ውስጥ ናቸው። የአማራ ኃይሎች በነበሩበት ጊዜ የትግራይ ደጋፊዎች ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች ዒላማ ይደረጉ ነበር። አሁን በትግራይ ኃይሎች ደግሞ የአማራ ደጋፊዎች ለሚባሉ ሰዎችም ተመሳሳይ ስጋት አለ። በአካባቢው ያሉ ሰዎች የሁለቱም ወገኖች ሰለባዎች ናቸው” ብሏል። 

የደቡብ ትግራይ ዞን አስተዳዳሪ ግን ወደ የተፈናቃዮቹ መመለስ የጸጥታ ስጋት እንደማይፈጥር እና መከላከያ ሠራዊት እና ፌዴራል ፖሊስ ፀጥታን የማስጠበቅ ኃላፊነት እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

ሆኖም የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነትን በመጥቀስ አካባቢዎቹ በቅርቡ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ስር እንደሚተዳደሩ ጠቁመው በአላማታ እና ኦፍላ የተቋቋመው የአማራ አስተዳደር ቀድሞውኑ መፍረሱን ገልጸዋል።

በአማራ በኩል ያለው ወገን አካባቢዎቹ ወደ ትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ስር መመለሱን እንደሚቃወሙ እና ህዝበ ውሳኔ እስከሚካሄድ ድረስ በመከላከያ ሠራዊት የሚመራ  የሽግግር አስተዳደር እንዲቋቋም ሀሳብ ማቅረቡን አዲስ ስታንዳርድ ተረድቷል።

እነዚህ አካባቢዎች የትግራይ ጦርነት በተቀሰቀሰ በሳምንታት ውስጥ በአማራ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የነበርውን የምዕራብ ትግራይን ያካትታሉ።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button