ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች በሲቪል ሰዎች ላይ መጠነ ሰፊና አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆኑን ኢሰመኮ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 26 ዓ/ም፦ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች በሲቪል ሰዎች ላይ መጠነ ሰፊና አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች፤ ግድያ፣ አካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀል እየደረሰ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ዛሬ ታህሳስ 26 ቀን ባወጣው መግለጫ በክልሎቹ  በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሰው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አሳሳቢነት በእጅጉ መቀጠሉን ገልጾ በተለይም በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ተስፋፍተው በቀጠሉት ግጭቶች ዐውድ ውስጥ ሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች፣ ማፈናቀሎች፣ እገታዎች እና ዘረፋዎች የነዋሪውን ሕይወት እጅግ የከፋ አድርገውታል ብሏል፡፡ 

ኢሰመኮ በመግለጫው በአማራ ክልል፣ በአዊ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር፣ በአየሁ ጓጉሳ ወረዳ፣ አምበላ ቀበሌ እና በዚገም ወረዳ ሶሪት ቀበሌ ከጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ቀናት በተፈጠረው ብሔር ተኮር ግጭት ሞት እና የአካል ጉዳት እንዲሁም በኢንቨስትመንት ቦታዎች ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል። በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ቡሬ ዙሪያ ወረዳ፣ ፈጣም ሰንቶም እና በቆጣቦ ቀበሌዎች ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. እና በኅዳር 1 ቀን 2016 ዓ.ም. “ኢመደበኛ የአማራ ታጣቂዎች” በሰነዘሩት ብሔር ተኮር ጥቃት በርካታ ሰዎች ላይ የሞት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ደርሷል ብሏል። በግጭቱም ምክንያት ነዋሪዎች ተፈናቅለው በቡሬ ዙሪያ ወረዳ በሚገኙ አጎራባች ቀበሌዎች እና ወደ ኦሮሚያ ክልል ለመሄድ መገደዳቸውና የቀንድ ከብቶች መዘረፋቸው መግለጫው አመላክቷል። 

በአርሲ ዞን፣ ሸርካ ወረዳ ስር በሚገኙ ቀበሌውች ማንነታቸው በውል ያልተለየ ታጣቂዎች በፈጸሙት ብሔር/ማንነት ተኮር ጥቃት በረካታ ሰዎች መገደላቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።

በተጨማሪም በክልሉ፣ ቄለም ወለጋ ዞን፣ ጊዳሚ ወረዳ፣ በቤጊ-ጊዳሚ ሲኖዶስ ጊዳሚ ሰበካ ሥር የምትገኘው የመናኮ መናሞ ቀበሌ የሃሞ ቶኩማ አጥቢያ የመካነ ኢየሱስ ቤተ-ክርስቲያን አባላት የነበሩት ዘጠኝ ምዕመናን፣ የቤተ-ክርስቲያኗ ሽማግሌዎች፣ የወጣቶች ኮሚቴ አባላት እንዲሁም ሌሎች አገልጋዮችን ኅዳር 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሌሊት 8፡00 ሰዓት አካባቢ እስካሁን ማንነታቸው ባልተለዩ በታጠቁ ቡድኖች ተገድለዋል ሲል ኮሚሽኑ አክሎ አስታውቋል።  

በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ አሶሳ ዞን፣ ኦዳ ብልድግሉ ወረዳ ሥር በሚገኙ ቤልሚሊ፣ አልከሻፊ እና ቤላደሩ ቀበሌዎች በሚኖሩ የቤኒሻንጉል ብሔር ተወላጆች እና አብረው በሚኖሩት የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ላይ ኅዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ-ሸኔ) ታጣቂ ቡድን አባላት በተፈጸመ ጥቃት አስራ ሰባት ሰዎች መገደላቸውንና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱንኢሰመኮ በመግለጫው አስታወቋል፡፡ 

ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ በክልሎቹ በሲቪል ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው ግድያ፣ አካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀል ተጠያቂነት ማረጋጋጥን ጨምሮ እየደረሰ ካለው ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ጋር የሚመጣጠን የፌዴራል መንግሥቱና የየክልሎቹን መንግሥታትን አፋጣኝ፣ ተጨባጭና ዘላቂ መፍትሔ የሚሻ ነው መሆኑን ጠቁሟል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በዚህ የግጭት ዐውድ እየደረሰ ያለው እጅግ አሠቃቂ ጉዳት ከዚህ የበለጠ ከመባባሱ እና የበለጠ ጉዳት ከመድረሱ በፊት መንግሥት ተገቢውን ሰላማዊና ፖለቲካዊ መፍትሔ ተግባራዊ እንዲያደርግ፣ ሁሉም ታጣቂ ቡድኖችና መንግሥት ሰብአዊ የተኩስ ማቆም አድርገው ወደ ውይይት እንዲያመሩ፣ መንግሥት በተለይ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰትና ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ አካባቢዎችና ነዋሪዎች በሙሉ የተሟላ ጥበቃና ደኅንነት እንዲያረጋግጥ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡ ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም “የጥፋተኞችን ተጠያቂነትና ፍትሕ ከማረጋገጥ በተጨማሪ፤ መንግሥትና ሌሎች አጋር አካላት በጥቃቶቹ ምክንያት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች በቂ የሆነ አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲያቀርቡ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንዲመቻች ማድረግ” አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button