ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ ኢትዮጵያ እስከ 2030 ከካርበን ሽያጭ 100 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት እየሰራች ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17/2016 .ም፡ ኢትዮጵያ በደን ልማት ዘርፍ እያከናወነች ባለው ሥራ እ.ኤ.አ እስከ 2030 ከካርበን ሽያጭ 100 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደምታገኝ ይጠበቃል ሲሉ የሀገሪቱ የደን ልማት ከፍተኛ ሃላፊ መናገራቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በዘገባው አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ ገቢውን ለማግኘት ያቀደችው ከካርበን ሽያጭ፣ ደንን ከጭፍጨፋ በመከላከልና በማልማት እንዲሁም የካርበን ልቀትን በመቀነስ በሚከናወኑ ስራዎች በሚገኝ አለም አቀፍ ክፍያዎች መሆኑን በኢትዮጵያ ደን ልማት ብሔራዊ የ”ሬድ ፕላስ” ፕሮግራም አስተባባሪ ይተብቱ ሞገስ (ዶ/ር) መናገረቻውን ዘገባው አመላክቷል።

በኢትዮጵያ ከደን ልማት ሥራ ባለፉት 10 ዓመታት ከአለም ባንክ እና ኖርዌን ከመሳሰሉ ሀገራት በተገኘ ክፍያ 150 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማምጣት እንደተቻለ ሃላፊው መናገራቸውን ዘገባው አካቷል።

ከተለያዩ የአለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በመሥራት ላይ እንገኛለን ሲሉ ሃላፊው ዶ/ር ይተብቱ ማናገራቸውን ያስነበበው ዘገባወ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል እየተከናወነ በሚገኘው የደን ጥበቃ ከዓለም ባንክ ጋር የ40 ሚሊዮን ዩሮ ክፍያ ስምምነት መደረሱን መናገራቸውን አስታውቋል።

የካርበን ሽያጭ ክፍያ የረጅም ጊዜ የደን ልማት ሥራን የሚጠይቅ መሆኑን እና ካርበን እንደማንኛውም እንደበቆሎ ወይም ቡና ዋጋ ወጥቶለት እንደ ገበያው ሁኔታ የሚሸጥና ገቢ የሚያስገኝ ዘርፍ ነው ሲሉ ማስረዳታቸውንም አካቷል።

ከዘርፉ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት በደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ክልል አንድ ሚሊዮን ሄክታር ደንን በመከለል በአካባቢው ለሚኖረው ማኅበረሰብ የኑሮ ማሻሻያ ድጋፍ በመስጠት እንዲያስተዳድሩት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል ብሏል፡፡

ኢትዮጵያ ብሔራዊ የካርበን ማዕከልን በማቋቋም በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ባለሙያዎችን አደራጅታ መሥራት ብትችል በየዓመቱ ከዘርፉ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላሮችን ማግኘት የምትችልበት ዕድል እንደሚፈጠር ማመላከታቸውንም ዘገባው አስታውቋል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button