ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የዘር ማጥፋት ወንጀል ስጋት የለም ሲል አስተባበለ፣ የመንግስታቱ ድርጅት አማካሪዋን መግለጫ ኮንኗል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1/2016 .ም፡ የመንግስታቱ ድርጅት ልዩ አማካሪ በኢትዮጵያ አሁንም የዘር ማጥፋት ወንጀል ከፍተኛ ስጋት አለ ሲሉ የሰጡት መግለጫ ሃላፊነት የጎደለው፣ በግዴለሽነት የተሰጠ እና የሀገሪቱን አሁናዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አጣጣለው።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ ልዩ አማካሪዋ ለመግለጫቸው ዋነኛ ማጣቀሻ ያደረጉት እና በኢትዮጵያ ላይ ተንኳሽ አገላለጽ እንዲጠቀሙ መነሻ የሆናቸው የአለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ኤክስፐርቶች በኢትዮጵያ (ICHREE) ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ያቀረበውን ሪፖርት ነው ሲል ተችቷል። የተመድ የባለሞያዎች ቡድን ተገቢነት ያለው ምርምራ በቦታዎቹ በመገኘት ሳያደርግ በርቀት ባገኘው ተአማኒነት በጎደለው መረጃ ተንተርሶ ነው ሪፖርቱን ያጠናቀረው ሲል የኮነነው መግለጫው የመንግስታቱ ድርጅት አማካሪዋ እንዲህ አይነት ሃላፊነት የጎደለውን ሪፖርት ዋቢ አድርገው መግለጫ መስጠታቸውን አግባብ አይደለም ብሏል።

ልዩ አማካሪዋ በፕሪቶርያ ከአንድ አመት በፊት የተፈረመው የሰላም ስምምነት ባመዛኙ አልተሳካም ማለት በሚቻልበት ደረጃ ላይ ይገኛል ማለታቸውን እንደማይቀበለው እና ፍጹም ሀሰት ነው ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መግለጫ ስምምነቱ በሰሜን ኢትዮጵያ የመሳሪያ ድምጽ እንዳይሰማ አድርጓል ሲል ገልጿል።

የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በመግለጫው ማገባደጃ ልዩ አማካሪዋ የተሳሳተ ያለውን መግለጫቸውን እንዲያርሙ ጠይቋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button