ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ የመኪና አደጋ በትግራይ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተፈትነው ሲመለሱ የነበሩ ስድስት ተማሪዎችን ህይወት ቀጠፈ፣ 53 ተማሪዎች ቆስለዋል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3/2016 ዓ.ም፡- በትግራይ ክልል የተሰጠውን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተፈትነው ወደ መጡበት ሲመለሱ የነበሩ ተማሪዎችን ጭኖ ሲጓዝ በነበረ አውቶብስ ላይ በደረሰ አደጋ በትንሹ የስድስት ተማሪዎችን ህይወት ሲያልፍ 53 ተማሪዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተገለጸ።

ፈተናቸውን በአዲግራት ዩኒቨርስቲ ተፈትነው ወደ መጡበት ተንቤን እና አከባቢዋ ሲመለሱ የነበሩትን ተማሪዎች ይዞ ይጓዝ የነበረው አውቶብስ አደጋ የደረሰበት ሀውዜን ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው አጽቢ በተባለች ቦታ መሆኑ ተገልጿል።

የሀውዜን ፍሬሰላም ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር አስመላሽ ተክለሃይማኖት ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት አራቱ ተማሪዎች አደጋው እንደደረሰ ወዲያውኑ መሞታቸውን አስታውቀው አንደኛው ተማሪ ወደ ሆስፒታል በመወሰድ ላይ እያለ መንገድ ላይ ህይወቱ ማለፉን እና ሌላ አንድ ተማሪ ደግሞ ሆስፒታል እንደደረሰ ህይወቱ ማለፉን ገልጸዋል።

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው 53 ተማሪዎች የህክምና አገልግሎት እንደተሰጣቸው የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ተማሪዎቹ የደረሰባቸው ጉዳት ከቀላል እስከ ከባድ መሆኑን አስታውቀዋል። ጉዳት ከደረሰባቸው ተማሪዎች መካከል 24ቱ ጉዳታቸው ከፍተኛ በመሆኑ መቀለ ወደሚገኘው አይደር እስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መላካቸውን ያስታወቁት አስመላሽ ቀሪዎቹ 29 ተማሪዎች ህክምና ተሰጥቷቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር በተደረሰ ስምምነት መውጣታቸውን አመላክተዋል።

በአይደር ሆስፒታል የድንገተኛ ክፍል ነርስ የሆነው አበበ ሃፍቱ ለአዲስት ስታንዳርድ እንዳስታወቀው 19 የሚሆኑ የእግር ስብራት እና ከፍተኛ ጉዳት በሰውነት አካላታቸው ላይ የደረሰባቸው ተማሪዎች ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛል። አንድ ተማሪ እጅግ አስጊ በሆነ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በትግራይ ለሁለት አመታት ከተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ ከመስከረም 29 እስከ ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም በክልሉ በተሰጠ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የመልቀቂያ ፈተና 9ሺ 514 ተማሪዎች በክልሉ በሚገኙ አራት ዩኒቨርስቲዎች ለፈተና መቀመጣቸውን የክልሉ የትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ኪሮስ ጉዑሽ አስታውቀዋል።

በሌላ ዜና በትግራይ ሀይሎች እና በፌደራል መንግስቱ መካከል ተካሂዶ በነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት ወቅት ህይወታቸው ያለፉ ተዋጊዎችን ለመዘከር የታወጀው የሶስት ቀናት ክልላዊ የሀዘን ቀን በሁሉም የክልሉ ከተሞች በመከበር ላይ ይገኛል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button