ቢዝነስዜና

ዜና፡ የደላላን ጣልቃ ገብነት በዘላቂነት እልባት ለመስጠት የሚያስችል መመሪያ እያዘጋጀ መሆኑን መንግስት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11/2016 .ም፡ ባለፉት 5 ወራት የግብይት ሰንሰለቱ ላይ እንቅፋት በመፍጠር የዋጋ ንረት እንዲባባስ ያደረጉ 790 ህገ- ወጥ ደላላዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስትሩ በማህበራዊ ሚዲያ ፌስቡክ ገጹ ባጋራው መረጃ እየተስተዋለ ላለው የዋጋ ንረት የግብይት ሰንሰለቱ መርዘም፣ የደላላዎች ጣልቃ ገብነት እና አላስፈላጊ ኬላዎች ተጠቃሽ መንስኤዎች መሆናቸውን ጠቁሞ እነዚህን ችግሮች በመፍታት የዋጋ ንረቱን ለማርገብ በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

ከሰራቸው ስራዎች መካከልም በግብርና ምርት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በቁም እንሰሳት እና በሰብል ምርቶች ግብይት ውስጥ የነበሩ ደላላዎችን ፈቃድ በመሰረዝ ከግብይት ሂደቱ እንዲወጡ ማድረጉን አስቀምጧል።

ባለፉት 5 ወራት በተደረገ ክትትልም እንደ ሀገር በግብይት ሂደቱ ውስጥ ተዋንያን ሆነው በተገኙ 790 ህገ-ወጥ ደላላዎች ላይ አስተዳደራዊ ርምጃ መውሰዱን ያስታወቀው ሚኒስቴሩ በቀጣይ የደላላን ጣልቃ ገብነት በዘላቂነት እልባት ለመስጠት የሚያስችል መመሪያ እያዘጋጀ መሆኑን ጠቁሟል።

አምራቾች ምርታቸውን ለሸማቹ በቀጥታ የሚያቀርቡበትን የገበያ መሰረተ-ልማት በማስፋፋት የግብርና ምርቶች በአምራች ህብረት ስራ ዩኒዮኖች እና በሸማቾች ማህበራት አማካኝነት እንዲቀርቡ በማድረግ የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት እየተሰራ እንደሚገኝ አመላክቷል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button