ዜና

ዜና፡ 'ግብፅ አፍሪካን ሊያምስ ከሚችለው ድርጊት እንድትቆጠብ' ኢትዮጵያ አሳሰበች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20/ 2016 ዓ/ም፦  ግብፅ አፍሪካን ሊያምስ ከሚችለው ድርጊት ተቆጥባ ወደ ትክክለኛው መስመር እንድትመለስ ኢትዮጵያ አሳሰበች።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ ተወካይ አምባሳደር ዮሴፍ ካሳዬ በድርጅቱ 79 ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ግብፅ የኢትዮጵያን በተፈጥሮ ሀብቷ ተጠቅማ የመልማት መብቷን የሚጋፋ አቋም ይዛለች ሲሉ ከሰዋል። 

ለናይል ወንዝ ጠብታ ውሃ የማታበረክተው ግብፅ የሌሎችን በውሃው የመጠቀም መብትን ስትጋፋ ከመኖሯም በላይ የጋራ አጠቃቀምን የተመለከቱ ትብብሮችን እየተቃወመች ትገኛለች ሲሉ አምሳደር ዮሴፍ ተናግረዋል።

በመንግስታቱ ድርጅት ጉባዔ ላይ የግብጽ ተወካይ ያሰሙት ንግግር የአንድን ሀገር የተፈጥሮ ሀብቷን ተጠቅማ የመልማት  መብቷን እና ይህን የሚደነግገውን ዓለም አቀፍ መርህ የሚቃረን ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በማንኛውም መልኩ ግብፅን ችግር ውስጥ የሚያስገባ እና የመልማት መብቷን የሚገድብ እንቅስቃሴ እና “የጥላቻ ተግባር” የመፈጸም ፍላጎት እንደሌላትም አምባሳደሩ አስታውሰዋል።

ግብፅ ወንዙን የሚያመነጩትን ሀገራት በተጋፋ መልኩ “በቅኝ ግዛት ውል” ውሃውን ለብቻዋ ስትጠቀም መኖሯን የጠቀሱት አምባሳደሩ ነገር ግን ኢትዮጵያ ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ወንዙን በትብብር እና በፍትሃዊነት እንዲጠቀሙ የጀመረችውን ጥረት ትቀጥላለች ብለዋል። 

ግብፅ ዘመኑ ያለፈበትን የቅኝ ግዛት ውሎችን ትታ ሁሉንም ተጠቃሚ ሊያደርግ ወደሚችለው ትብብር እንድትመጣ ጥሪ አቅርበው፣ ይህን አውነታ የምትቀበልበትና ትብብር ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት የምትረዳበት ጊዜ ይመጣል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የጋራ የሆነውን ሀብት ለብቻዬ ካልተቆጣጠርኩ የሚለው “ያፈጀና ያረጀ አስተሳሰብ” የማይሰራ ነው ሲሉ አምባሳደሩ አስረድተዋል።

ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርገው የትብብር ጊዜ አሁን ነው ያሉት አምባሳደር ዮሴፍ፣ ግብፅም አማራጭ ወደ ሌለው የትብብር ማዕቀፍ እንድትመለስም ጥሪ አቅርበዋል።

በዓባይ ወንዝ ላይ የገነባው የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአሁኑ ጊዜ የቀጣናውን ሀገራት በኃይል አቅርቦት ማስተሳሰር መጀመሩንም ተናግረዋል።

የዓባይ ወንዝ አንድ ሦስተኛውን የኢትዮጵያ ክፍል የሚያካልል እና ከ75 በመቶ በላይ የውሃ ምንጩ ከኢትዮጵያ ቢሆንም ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት በምግብ ዋስትና እና በኃይል አቅርቦት ችግሮች ስትፈተን መኖሯን ገልጸዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

አምባሳደር ዮሴፍ ካሳዬ አክለውም 120 ሚሊዮን ገደማ ከሚሆነው ሕዝቧ ከግማሽ የማያንሰው በንጹህ ውሃ እጥረት እና በኃይል አቅርቦት ችግር ውስጥ እየኖረ ይህን ችግር ለመፍታት እጇን አጣምራ ትቀመጥ ማለት ፍትሃዊነት እንዳልሆነም ተናግረዋል።

ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተሻለ ህይወት መሥራት ቅድሚያ ተግባራችን ነው ያሉት አምባሳደሩ ይህን ለማድረግ ግን ኢትዮጵያ የማንንም የመልማት መብት እንደማትገፋ እና የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በጋራ የመጠቀም መርህን እንደምታከብር ገልጸዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button