ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: መንግስት በአማራ ክልል የህግ ማስከበር ዘመቻ እያካሄድኩ ነው ሲል ገለጸ፣ አምነስቲ በበኩሉ የዘፈቀደ እስር እየተከናወነ ነው ሲል ኮንኗል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22/2017 ዓ.ም፡- መንግስት በአማራ ክልል ባለፉት ቀናት እያካሄደ ያለው የዘፈቀደ እስር በሀገሪቱ የህግ የበላይነት በከፍተኛ ሁኔታ እየተሸረሸረ መሆኑን ያሳያል ሲል አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ትላንት መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ተቸ።

መንግስት በበኩሉ በአማራ ክልል የህግ የማስከበር ዘመቻ ነው እያካሄድኩ ያለሁት ሲል በመግለጽ “ሕግ የማስከበር ሂደቱ የሚቆመው የክልሉ ሰላም ሙሉ በሙሉ ሲረጋገጥ ነው” ብሏል።

የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች “በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የትምህርት ተቋማት ሰራተኞችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን በዘፈቀደ አስረዋል፣ በሀገሪቱ ህግ መሰረት በ48 ሰዓታት ፍርድ ቤት መቅረብ ሲገባቸው አልቀረቡም” ሲል ኮንኗል።

“የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊቱ እና ፖሊስ በክልሉ እያካሄደው ያለው የዘፈቀደ እስር የሀገሪቱ መንግስት ለህግ የበላይነት ቦታ እንደማይሰጥ ተጨማሪ ማሳያ ነው” ሲል አምነስቲ ገልጿል።

“የመንግስት ባለስልጣናት የፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ሳይኖራቸው የነዋሪዎችን ስም ዝርዝር በመያዝ ብቻ በዘፈቀደ እንደሚያስሩ የአይን እማኞች ነግረውኛል” ያለው አምነስቲ “ለእስር ከተዳረጉት ሰዎች መካከል በሀገሪቱ ህግ መሰረት በ48 ሰዓታ ፍርድ ቤት የቀረቡ የሉም” ሲል ጠቁሟል።

የመንግስት ባለስልጣናት በክልሉ የሚፈጽሙትን የዘፈቀደ እስር በአፋጣኝ እንዲያቆሙ የጠየቀው አምነስቲ “አለም በሚያውቃቸው ወንጀሎች ፈጽመው ከሆነ በዚሁ አግባብ ክስ ይመስረትባቸው፣ አለበለዚያ ደግሞ በአፋጣኝ ሊፈቱ ይገባል” ሲል አሳስቧል።

የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት “የዘፈቀደ እስር መፈጸምን እንደ መጨቆኛ መሳሪያ የሚጠቀሙበት አግባብ መቆም አለበት” ሲል አስታውቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተያያዘ ዜና መንግስት በአማራ ክልል ሕግ የማስከበር እርምጃ እየተወሰድኩ ነው ሲል ትላንት መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም ባህርዳር ላይ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፤ በክልሉ በመካሄድ ላይ ስላለው ዘመቻ ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊት ኮሎኔል ጌትነት አዳነ እና የክልሉ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር መንገሻ ፈንታው በጋራ በመሆን ነው።

የመከላከያ ሠራዊት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊት ኮሎኔል ጌትነት አዳነ “በክልሉ ሁከት እና ብጥብጥን ለማስቆም ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን ችግር በሚፈጥሩ የታጠቁ ሀይሎች እና በመንግስት መዋቅር ላይ በሚገኙ አካላት እርምጃ መወሰድ መጀመሩን” ገልጸዋል።

“ባለፉት ቀናት ባካሄድናቸው ኦፐሬሽኖች የከተማ ሴሉ በአልን እንደምክንያት በመጠቀም ወደ ገጠር የመሸሽ፣ ከግጭት እራስን አርቆ ወደ ተመረጡ ኮሪደሮች መሰባሰብ፣ በማህበራዊ ሚዲያ ውዥንብር መንዛት” እየተካሄደ ነው ሲሉ ኮለኔሉ ገልጸዋል።

የኦፕሬሽኑ ዓላማ ሁከትን እና ብጥብጥን አስወግዶ ለክልሉ መንግሥት እና ሕዝብ ሰላምን ማስፈን ነው ያሉት ኮሎኔል ጌትነት አዳነ “ሕግ የማስከበር ሂደቱ የሚቆመው የክልሉ ሰላም ሙሉ በሙሉ ሲረጋገጥ ነው” ብለዋል።

መከላከያ “የአማራን ሕዝብ ስለሚያከብር የክልሉ መንግሥት የጀመረው የሰላም ጥረት ዳር እንዲደርስ የሚችለውን ሁሉ አድርጓል” ያሉት ኮሎኔል ጌትነት ከመንግሥት ጋር በሰላማዊ መንገድ የሚነጋገሩ ካሉ በሮቹ ያልተዘጉ ቢኾኑም መከላከያ ግን ሕግ ማስከበሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

“ወታደራዊ ኦፕሬሽኑ በሚገባ የተጠና ነው ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ንጹሐንን ለመጠበቅ ሲባል በጥንቃቄ ይመራል” ሲሉም ገልጸዋል።

“በምንም መንገድ ቢኾንም ግን መንገድ ዝጉ እና ተማሪዎች አይማሩም ከሚል ጽንፈኛ ቡድን ጋር ከዚህ ያለፈ ትዕግስት አይኖርም” ሲሉ ተናግረዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button