ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ የትራንስፖርት ማህበራትን መልሶ ለማደራጀት እና ያረጁ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ለማገድ በወጣው መመሪያ ምክንያት ሚኒስቴሩ ከከባድ የጭነት ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ጋር አለመግባባ ውስጥ ገባ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22/ 2017 ዓ/ም፦ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፤ ትራንስፖርት ማኅበራትን መልሶ ለማደራጀት እና በርካታ አመታት ያገለገሉ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ለማገድ ከአንድ ዓመት በፊት በወጣው አስገዳጅ መመሪያ ምክንያት ከከባድ የጭነት ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ጋር አለመግባባት ውስጥ ገባ። 

የትራንስፖርት ማኅበራት ወደ አክሲዮን ማኅበር ወይም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር (ኃ.የተ.የግ.ማ.) እንደገና እንዲዋቀሩ የሚደነግገው መመሪያ ነው ውዝግብ ያስከተለው። 

መመሪያው ከ30 ዓመታት በላይ ያገለገሉ ድንበር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች ቀስ በቀስ ስራ እንዲያቆሙ የሚደነግግ በመሆኑም አለመግባባቱ ተባብሷል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የጭነት ትራንስፖርት ኦፕሬተሮች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ችግሩ የተፈጠረው አስፈጻሚ አካላት መመሪያውን በብቃት ባለመወጣታቸው ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

“ባለፈው አመት ከሚኒስቴሩ የስራ ኃላፊዎች ጋር ባደረግነው ውይይት መመሪያው አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝበናል” ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ ነገር ግን አሁን ላይ የአዋጁን አተገባበር በተመለከተ አለመግባባት መፈጠሩን ገልጸዋል። 

የኮንቲኔንታል ትራንስፖርትና አጠቃላይ ንግድ ኃ.የተ.የግ.ማ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አቡበከር ሰኢድ በሁለቱ ወገኖች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት አብራርተዋል።  

“በመጀመሪያ የትራንስፖርት ማህበራቱን መልሶ ለማዋቀር ከመታቀዱ በፊት የተጠየቅነው አንድ መኪና ብቻ ነበር” ሲሉ የገለጹት አቶ አቡበከር “ነገር ግን አሁን ላይ ኃላፊዎች ተጨማሪ ተሽከርካሪዎችን እንድንገዛ ትእዛዝ ሰጥተዋል ይህ ደግሞ በአቅማችን ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል” ሲሉ ተናግረዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በሚኒስቴሩ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ይርጋ ታደሰ በቅርቡ በሰጡት ገለጻ የውዝግቦቹ መነሻ የሆነው ወደ አዲሱ የንግድ አደረጃጀት ያልተሸጋገሩ የትራንስፖርት ማህበራት መመሪያውን እንዲያከብሩ ለማድረግ እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች ምክንያት ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በመመርያው መሰረት ወደ አዲሱ የንግድ አደረጃጀት ያልገቡ የትራንስፖርት ማህበራት ወደ አዲሱ አደረጃጀት እንዲገቡ ቀነ ገደብ ቢሰጣቸውም አብዛኞቹ መስፈርቱን ማሟላት አለመቻላቸውን ጠቁመዋል።

የቀድሞ የትራንስፖርት ማህበራትን ወደ አክሲዮን፣ ኃ/የተ/ግ/ማ እና የግል ድርጅት በሚል አደረጃጀት እንዲደራጁ የሚደነግገው መመሪያ በግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. የወጣ ነው። 

መመርያው ይፋ የተደረገው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ የመንገድ ትራንስፖርት አዋጅን በ2014 ዓ.ም. ካፀደቀ ከአንድ አመት በኋላ ሲሆን ሚኒስቴሩ የጭነት እና የመንገደኞች ትራንስፖርት ዘርፉን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመቆጣጠር መመሪያ የማውጣት ስልጣን ተሰጥቶታል። 

“መመሪያው ከመውጣቱና ወደ ትግበራ ከመገባቱ በፊት ከባለድርሻ አካላት ጋር በተለያዩ መድረኮች ውይይት ተደርጎ ስምምነት ላይ ተደርሷል” ሲሉ አቶ ይርጋ ተናግረዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት የጭነት ትራንስፖርት ኦፕሬተሮች ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ ከጭነት ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ጋር በተደረገው ውይይት የትራንስፖርት ማህበራትን ወደ  ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መልሶ የማደራጀት አስፈላጊነት ላይ መግባባት ላይ መደረሱን ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

“ሆኖም ግን መመርያውን ማስፈጸም ያለባቸው ሰዎች ህጉን ሙሉ በሙሉ አልተረዱትም” ብለዋል።

ባለፈው አመት የወጣው መመሪያ ከ30 አመት በላይ የሆናቸውን ድንበር አቋራጭ ተሽከርካሪዎችን ቀስ በቀስ ለማስወገድ እንዲሁም ዘመናዊ የሆኑትን እና ከፍተኛ አፈጻጸም ያላቸውን ተሽከርካሪዎች ለማሳደግ ያለመ ነው ተብሏል።

አቶ ይርጋ በበኩላቸው “የአገሪቱ የወጪ ገቢ ንግድ እየጨመረ መምጣቱ እነዚህን ያረጁ ተሽከርካሪዎችን ለመጠቀም እና ዕቃዎችን በብቃት ለማጓጓዝ አስቸጋሪ አድርጎታል” ብለዋል ።

የትራንስፖርት ማህበራቱ ዋና ስራ አስኪያጅ በበኩላቸው በዚህ ሃሳብ የሚስማሙ ሲሆን ከ30 ዓመት በላይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ረጅም ርቀት ለመጓዝ አስቸጋሪ በመሆናቸው በአዲስ ተሽከርካሪዎች መተካት አለባቸው ይላሉ።

በተጨማሪ ከአየር ብክለት ስጋት ጋር ተያይዞ አሮጌ ተሽከርካሪዎችን በአዲስ ለመተካት መታቀዱንም አስረድተዋል።

“ይሁን እንጂ፣ ባለንብረቶች ያረጁ ተሽከርካሪዎቻቸውን በአዲስ ለመተካት እንዲችሉ ከመንግስት በኩል የተደረገ ድጋፍ የለም” ሲሉ ዋና ሥራ አስኪያጁ አጽንኦት ሰጥተዋል። አክለውም “በአሁኑ ጊዜ ኃላፊነቱን እንዲወስድ የሚጠበቀው የተሽከርካሪው ባለቤት ነው” ብለዋል።

በመላ ሀገሪቱ ከ12,500 በላይ የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከ100 በላይ በሚሆኑ ማህበራት ስር ተደራጅተው በመስራት ላይ ይገኛሉ።

ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ቆይታ ያደረጉ እና፣ ወደ ጅቡቲ ወደብ አዘውትረው የሚጓዙት የከባድ ጭነት መኪና ሹፌር በበኩላቸው እንደገለጹት፣ እሳቸውና ሌሎች አሽከርካሪዎች ለ30 ዓመታት እና ከዚያ በላይ አገልግሎት ላይ የቆዩ ተሽከርካሪዎችን ስለመተካት መረጃ እንዳልተነገራቸው ጠቁመዋል።

“በዚህ ጉዳይ ማንም አላወያየንም። ምናልባት ይሄ የተሽከርካሪዎቹን ባለንብረቶች የሚመለከት ነገር ይመስለኛል” ብለዋል።

መንግስት ከ30 ዓመት በላይ ያገለገሉ ተሸከርካሪዎችን ለማቀብ እንዲሁም የትራንስፖርት ማኅበራትን መልሶ ለማደራጀት ማቀዱን ተከትሎ የተፈጠረው ውዝግብ የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ሳይሰጣቸው እንዲቆዩ አድርጓል።

ባሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የደንበኞች ጥያቄ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ገልጾ፤ በየቀኑ ከ1,100 በላይ የጭነት ትራንስፖርት ኦፕሬተሮች የብቃት ማረጋገጫ ማመልከቻዎች እያቀረቡ መሆናቸውን ገልጿል።

ሚንስቴሩ የጅቡቲ የመግቢያ ፍቃድና ሌሎች አገልግሎቶችን ፍላጎት ለማሟላት የሰራተኞች ቁጥር መጨመሩን እና የአገልግሎት ሰዓታትን ከመደበኛ የስራ ሰዓታት በላይ ማራዘሙንም አስታውቋል።

መመሪያው ቢወጣም ከ30 ዓመታት በላይ ያገለገሉ የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ጅቡቲ የመግቢያ ፍቃድ እየተሰጣቸው መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

በአሁኑ ጊዜ እቃዎችን ወደ ጅቡቲ ወደብ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች ላይ እጥረት አለመኖሩንም አመላክተዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button