ህግ እና ፍትህዜና

ዜና፡ በጎንደር ከተማ ዙርያ በተፈጸሙ የከባድ መሣሪያ ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22/2017 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል፤ ጎንደር ከተማ ዙርያ በሚገኙ አከባቢዎች “በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች” ተፈጸሙ በተባለ በከባድ መሳሪያ የታገዙ ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።

ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ደምበያ ወረዳ አይምባ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት በመንግስት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካክለ እየተካሄደ ባለው ግጭት፤ “የመንግስት ኃይሎች እሁድ መስከረም 19 ቀን 2017 ዓ.ም. በፈጸሙት በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ከ20 በላይ ሰዎች ተደግለዋል”።

“የመንግሥት የጸጥታ አካላት አዘዞ ካምፕ ላይ ሆነው ነው ዙ-23፣ ቢ-ኤም እና ሞርታር እየተኮሱ የነበረው” ያሉት ነዋሪው፤ በወቅቱ ከአይምባ ወደ አማኑኤል ወደሚባል ቦታ በመሸሽ ላይ የነበሩ ሰላማዊ ሰዎች ተመትተው መገደላቸውን ተናግረዋል።

ነዋሪው አክለውም “በእሁዱ ዕለት ጥቃት በትንሹ 20 የሚደርሱ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፤ ከተገደሉት በተጨማሪ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ 3 ግለሰቦችም ቆስለዋል” ብለዋል።

አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው ሌላ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ጎንደር ከተማ ነዋሪ በኩላቸው ከሰሞኑ በተለያዩ የጎንደር አከባቢዎች የአየር ድብደባን ጨምሮ ውጊያዎች መደረጋቸውን ገልጸዋል።

በደቡብ ጎንደር የተለያዩ ስፍራዎች ዛሬም ድረስ የቀጠሉ ከባባድ ውጊያዎች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን በስፍራዊ ከሚኖሩ ቤተሰቦቻቸው እንደሰሙ ነዋሪው ጠቁመዋል።

“የአየር ድብደባ መኖሩን ከቤተሰብ ነው የሰማነው። በተለይ ደቡብ ጎንደር እብናት፤ ጋይንት እና ክምር ድንጋይ አከባቢዎች ነበሩ በአየር የተደበደቡት። አብዘሃኛውን ጊዜ ተራራውን ነው የሚደበድቡት። ንጹሐን መኖርያ አከባቢዎች ላይ የተጣሉ ቦምቦች መኖራቸውንም ሰምተናል” ያሉት ነዋሪ አክለውም ውጊያዎች አሁንም በመደረግ ላይ በመሆናቸው የተገደሉ ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር ይሄን ያህል ነው ለማለት እንደማይቻል ገልጸዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተጨማሪ በዛሬው ዕለት ከጠዋት ጀምሮ በደቡብ ጎንደር ዞን የተለያዩ አከባቢዎች በተለይ ክምር ድንጋይ በተባለ አከባቢ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከባድ ውጊያ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በጎንደር ነዋሪ የሆኑ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሌላኛው ነዋሪ በበኩላቸው ከነገ መስከረም 23/ 2016 ዓ.ም. አንስቶ በመላው የአማራ ክልል አከባቢዎች የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እቀባ ላልተወሰነ ጊዜ እንደሚኖር የሚገልጹ ወረቀቶች መበተናቸውን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል መንግስት በበኩሉ በክልል ሕግ የማስከበር እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስታውቋል

ትላንት መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ እና የክልሉ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር መንገሻ ፈንታው በጋራ በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የመከላከያ ሠራዊት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ “በክልሉ ሁከት እና ብጥብጥን ለማስቆም ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን ችግር በሚፈጥሩ የታጠቁ ሀይሎች እና በመንግስት መዋቅር ላይ በሚገኙ አካላት እርምጃ መወሰድ መጀመሩን” ገልጸዋል።

“ወታደራዊ ኦፕሬሽኑ በሚገባ የተጠና ነው” ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ንጹሐንን ለመጠበቅ ሲባል “በጥንቃቄ ይመራል” ሲሉም ገልጸዋል።

“በምንም መንገድ ቢኾንም ግን መንገድ ዝጉ እና ተማሪዎች አይማሩም ከሚል ጽንፈኛ ቡድን ጋር ከዚህ ያለፈ ትዕግስት አይኖርም” ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል የማዕከላዊ ጎንደር ዞን መቀመጫ በሆነችው ጎንደር እና በተለያዩ አካባቢዎች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በነበረው ግጭት “የጸጥታ አባላትን” ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን መዘገባችን ይታወሳል

በወቅቱ በነበረው ግጭት የትራንስፖርት አገልግሎቶች ተቋርጠው የነበረ ሲሆን የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ተዘግተው መቆየታቸው ይታወሳል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button