ዜናፖለቲካ

ዜና፡ በአላማጣ ከተማ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት 2 ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች 11 ቆሰሉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22/ 2017 ዓ/ም፦ በአላማጣ ከተማ ትናንት መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም. በምድረ-ገነት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አከባቢ በተሰበሰቡ ወጣቶች ላይ “ከትግራይ ኃይሎች ጋር ግንኙነት አላቸው” በተባሉ የታጠቁ ግለሰቦች በተሰነዘረ ጥቃት ሁለት ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች አስራ አንድ ሰዎች መቁሰላቸው ተገለጸ።

ጥቃቱ የተፈፀመው ትምህርት ቤቶች በመከፈታቸው ምክንያት በተቀሰቀሰ ተቃውሞ እንደሆነ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

“በአላማጣ ከተማ ትምህርት ቤቶችን መክፈት አስፈላጊ ሆኖ ሳለ አንዳንድ ነዋሪዎች በተለይም ወጣቶች ትምህርት ቤት መከፈቱን ተቃውመዋል” ያሉት ነዋሪ አክለውም ወጣቶቹ በአማራ ክልል ያሉ ግጭቶች እልባት እስኪያገኙ ድረስ ትምህርት ቤቶች መዘጋት አለባቸው ሲሉ መሟገታቸውን ጠቁመዋል።

ታጣቂዎቹ ቀበሌ 03 በሚገኘው ምድረ-ገነት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውጪ በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ ተኩስ እንደከፈቱ የአይን እማኙ ገልጸዋል።

እንደ ነዋሪው ገለጻ ከሆነ በጥቃቱ ከቆሰሉ ግለሰቦች መካከል ሰባቱ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ሆኖም የፌደራል የጸጥታ አካላት እስካሁን ምንም አይነት እርምጃ እንዳልወሰዱ ሲሉ ገልጸዋል።

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህር በበኩላቸው ክስተቱ በክልሉ ያለውን ውጥረት እንዳባባሰው ገልጸዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በትምህርት ጉዳይ ላይ ግጭት ውስጥ መግባት ተገቢ አይደለም ያሉት መምህሩ በክልሉ ሰላም እስካለ ድረስ ትምህርት መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

መምህሩ፤ የትምህርት ቤቶችን መከፈት የሚቃወሙ አካላት መደበኛውን የመማር ማስተማር ሂደት እንደሚያስተጓጉሉ ገልጸው፤ ይህም “በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ካሉ እኩዮቻቸው ጋር ያለው የትምህርት ሂደት ሊያደናቅፍ ይችላል ብለዋል”።

በአላማጣ ከተማ ተመሳሳይ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

በሰኔ 2016 ዓ.ም በደቡብ ትግራይ ዞን የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች “የህወሀት ታጣቂዎች” አንድ የመብራት ኃይል ሰራተኛን ገድለዋል በሚል የተከሰተውን ተቃውሞ ተከትሎ አንድ ሰው ሲገደል ሌሎች ሶስት ሰዎች መቁሰላቸውን መዘገባችን ይታወሳል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button