ዜናፖለቲካ

ዜና: የትግራይ እና አፋር ክልል ተፈናቃዮችን በአፋጣኝ ወደ ቀያቸው ለመመለስ ስምምነት መደረሱን አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23/2017 ዓ.ም፡- በትግራይ ተካሂዶ በነበረው ጦርነት ሳቢያ ከትግራይ እና ከአፋር ክልል የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ወደ ቀያቸው በአፋጣኝ ለመመለስ በሁለቱ ክልሎች መካከል ስምምነት መደረሱ ተገለጸ።

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የተመራ የክልሉ ልዑክ ትላንት መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም በሰመራ ጉብኝት አካሂዷል፣ ከአፋር ክልል ፕሬዝዳንት አወል አርባ እና ከክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋርም መክሯል።

አቶ ጌታቸው ረዳ በማህበራዊ ሚዲያ የኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ውይይታቸው በዋናነት ያጠነጠነው “የሁለቱን ህዝቦች ታሪካዊ የወንድማማችነት ግንኙነት ወደነበረበት ለመመለስ በሚቻልበት መንገድ፣ የሁለቱን ክልሎች የጋራ ደህንነት በማስጠበቅ፣ ሰላምና ልማትን ለማስፈን” በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ነው ብለዋል።

“የተቀዛቀዘውን የክልሎቹን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በአፋጣኝ ለማስጀመር ስምምነት ላይ ደርሰናል” ሲሉም ገልጸዋል።

“በመካከላችን የነበረውን የሻከረ ግንኙነት በማስቀረት ቀድሞ ወደ ነበረበት መልካም ግንኙነት ለመመለስ እና በሙሉ ልብ ለመስራት ተስማምተናል” ያሉት አቶ ጌታቸው “ሁለቱን ክልሎች የሚያገናኙ የተዘጉ መንገዶች እንዲከፈቱ፣ በሁለቱ ክልሎች መካከል ተቋርጦ የነበረው መደጋገፍ እንደገና እንዲጀመር ተስማምተናል” ሲሉ አስታውቀዋል።

“በትግራይና በአፋር ክልል ውስጥ የሚገኙ ጥያቄ ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶችን ወደ ሰላሙ ውይይት እንዲመለሱ ለማድረግ እና ለዚህም በጋራ ለመስራት” ተስማምተናልም ብለዋል።

“የከፋ ወንጀል በአንዱ ክልል ሰርተው በአንዱ ክልል ለመደበቅ የሚሞክሩ ተጠርጣሪዎችን፣ ህጋዊ በሆነ መንገድ የሚስተናገዱበት ሁኔታዎች ለመፍጠር ስምምነት ላይ ደርሰናል” ሲሉም ገልጸዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ለስምምነቶቹ ተግባራዊነት በየደረጃው ያሉ የስራ ሃላፊዎች በየጊዜው ተገናኝተው እንዲሰሩ ተስማምተናልም ብለዋል።

በውይይቱ ወቅትየአፋር ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በሁለቱ ክልሎች መካከል ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማጠናከር እንደሚሰራ ገልጸው፤ የአፋር ክልል የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ ነው ሲሉ መግለጻቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

በሁለቱ ክልል ህዝቦች መካከል የቆየ ወንድማማችነትን ለማጠናከር እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን ማሳደግ አስፈላጊ ነው ማለታቸውንም አስታውቋል።

በትግራይ ለሁለት አመታት በተካሄደው ጦርነት ወቅት የአፋር ክልል ከፌደራል መንግስቱ ጎን በመሰለፍ መዋጋቱ ይታወሳል። በጦርነቱ ወቅት ወደ ትግራይ ክልል የእርዳታ እህል በተቆራረጠ መልኩ ይገባ የነበረው በአፋር ክልል እንደነበር ይታወሳል።

ሁለቱም ክልሎች በሚጋሩባቸው ወሰኖች አከባቢ በርካታ ቁጥር ያለው ነዋሪ መፈናቀሉን በወቅቱ መዘገባችን ይታወሳል።

በናሳለፍነው አመት 2016 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ትግራይ ክልልን ከአፋር ክልል ጋር በሚያዋስነው በደቡብ ትግራይ በራያ አዘቦ ወረዳ ባደረሱት ጥቃት ህጻናትን ጨምሮ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን የወረዳው ሃላፊ ተዘራ ጌታሁን ማስታወቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ጥቃቱ የተፈጸመው እና ንጹሃኑ የተገደሉት “ኢሊጎባ” ተብላ በምትጠራ መንደር ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ሰኞ ሌሊት በተኙበት ነው ያሉት ሃላፊው ጥቃት አድራሾቹ “የአፋር ታጣቂዎች ናቸው፣ በጥቃቱም የ11 አመት ህጻንን ጨምሮ ሰባት ሰዎች ህይወታቸው አልፏል” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ መግለጻቸውን በዘገባው ተካቷል።

ጥቃቱን ተከትሎ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ ባወጣው መግለጫ “በራያ አዘቦ ወረዳ ከብት በመጠበቅ ላይ የነበሩ ወገኖቻችን በግፍ ተጨፍጭፈው ሞተዋል” ብሏል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button