ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና: በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራችን መልሱን እያሉ ይገኛሉ፣ መንግስት በበኩሉ ሁሉንም መንገድ ተጠቅሜ ለመመለስ እየሰራሁ ነው ብሏል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23/2017 ዓ.ም፡- እስራኤል በሊባኖስ እያካሄደች ባለችው ዘመቻ በቀጠናው ያለው የጸጥታ ስጋት እና ውጥረት ማየሉን ተከትሎ በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ በመጠየቅ ላይ መሆናቸው ተገለጸ።

እስራኤል በሊባኖስ በሚንቀሳቀሱ የሄዝቦላህ ታጣቂዎች ላይ እየፈጸመች ባለችው ጥቃት ለከፍተኛ ሰቆቃ እና መረበሽ መዳረጋቸውን ከቪኦኤ ጋር ቆይታ ያደረጉ በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል።

በሊባኖስ ነዋሪ የሆኑት እና በሞግዚትነት የሚተዳደሩት አረጋሽ ቱፋ ከአሜሪካ ድምጽ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት በአየር ድብደባው ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት ቀያቸውን ለቀው መፈናቀላቸውን አስታውቀዋል።

የአየር ጥቃቱን ተከትሎ“እጅግ አስፈሪ ድምጾች”ን እንደሚሰሙ የገለጹት ነዋሪዋ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበት መንገድ እንዲመቻችላቸው ተማጽነዋል።

ላለፉት አራት አመታት በቤሩት የቤት ሰራተኛ ሆና ስትሰራ መቆየቷን ያስታወቀቸው ሌላዋ ኢትዮጵያዊት መዲና ሃይሌ “ሁላችንም በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ነን፤ ፍንዳታዎች የዕለት ተዕለት ገጠመኞች ሆነዋል” ስትል ገልጻ አሁን ላይ በህይወቷ ተስፋ መቁረጧንና ለከፍተኛ ፍራቻ መዳረጓን ተናግራለች።

በሊባኖስ እንክብካቤ በመስጠት ለስድስት ዓመታት መቆየቷን የጠቆመችው ሰላማዊት ተስፋዬ እስራኤል በደቡብ ምስራቅ ሊባኖስ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ሁለት ኢትዮጵያውያን ሴቶች መገደላቸውን ለቪኦኤ አስታውቃለች።

የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ በሊባኖስ በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የብሔራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እንደገለጹት ኮሚቴው በሊባኖስ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን የተገኙ አማራጮችን ሁሉ በመጠቀም ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።

ኮሚቴው በቤይሩት በሚገኘው ቆንስላ ጄኔራል ጽሕፈት ቤት እየተካሄደ ያለውን የዜጎችን ምዝገባ የገመገመ ሲሆን የምዝገባ ሂደቱን በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ በመደገፍ ሰፊ ርብርብ እንዲደረግ አቅጣጫ መቀመጡን ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከዚህ ቀደም እስራኤል በሊባኖስ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ በደቡብ እና በምስራቅ የሊባኖስ አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስማቸውን፣ የፓስፖርት እና ስልክ ቁጥራቸውን  እንዲያስመዘግቡ በቤሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል ጽሕፈት ቤት ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በበኩሉ በሊባኖስ በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ በአገሪቱ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደኀንነት ላይ ችግር እንዳይደርስ በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝ አሳውቋል።

ሊባኖስ ከ250,000 በላይ ስደተኞች የሚኖሩባት ሃገር ስትሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ አብዘሃኛዎቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ተጠቁሟል።

እስራኤል በሊባኖስ በሚንቀሳቀሱት የሄዝቦላህ ታጣቂዎች ላይ የአየር ጥቃትን ጨምሮ በእግረኛ ጦር የታገዘ ዘመቻ ከፍቻለሁ ማለቷን ተከትሎ በቀጠናው ያለው ውጥረት ተባብሷል።

በተጨማሪ ኢራን መስከረም 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ በርካታ ሚሳኤሎችን ማስወንጨፏን ተከትሎ ውጥረቶች አይለዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button