“መንግስት በርከት ያሉ ድሃ ተኮር ፖሊሲዎች ሊያወጣ ይገባል” – አሜሪካና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ 17 ሀገራት

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3/2016 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ የሚካሄደው የሰብአዊ እርዳታ ግቡን ይመታ ዘንድ የፌደራል መንግስቱ ድሃ ተኮር የሆኑ ፖሊሲዎች ላይ እንዲያተኩር፣ በጀቶቹን አስቸኳይ ለሆኑ የሰብአዊ ችግሮች እንዲጠቀም ተጠየቀ።

ጥያቄውን ያቀረቡት አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ 17 ሀገራት ናቸው።

በኢትዮጵያ የተከሰተውን ሰብአዊ ቀውስ ለመቅረፍ ያስችል ዘንድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ፣ የኢትዮጵያ መንግስት እና ዩናይትድ ኪንግደም በጋራ በመሆን በቀጣይ ሳምንት ማክሰኞ ሚያዚያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አዘጋጅተዋል።

አሜሪካና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ 17 ሀገራት በጉዳዩ ዙሪያ ያላቸውን የጋራ አቋም የሚያንጸባርቅ መግለጫ አውጥተዋል። በመግለጫቸውም በሀገሪቱ ስለተከሰተው የሰብአዊ ቀውስ እና አጠቃላይ ሁኔታ አትተዋል።

በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች ሰብአዊ ችግሮች መከሰታቸውን ያስታወቀው መግለጫቸው ድርቅ፣ ግጭቶች፣ በሽታዎች እና ሌሎች ተጠቀቃሽ ምክንያቶች መንስኤ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የዜጎች ደህንነት በበርካታ የሀገሪቱ ክፍልም አለመረጋገጡን አስታውቀዋል። በ2023 የእርዳታ አቅርቦቱ ላልታለመለት አላማ እየዋለ መሆኑ መጋለጡን ተከትሎ በለጋሾች ዘንድ ያለውን እምነት መሸርሸሩን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ወዳጆች እና አጋር ሀገራት የፌደራል መንግስቱ ለተረጂዎች የእርዳታ እህል እንዲቀርብ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት እውቅና ይሰጣል ሲሉ ገልጸዋል። የተዘጋጀውን የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም እንደሚደግፉ እና አለምአቀፉ ማህበረሰብ ትኩረት እንዲሰጠው እንዲሁም የተቻለውን ድጋፍ እንዲያደርገ ለማበረታት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም አስታውቀዋል።

የሰብአዊ እርዳታው ግቡን ይመታ ዘንድ የፌደራል መንግስቱ ሊያደርጋቸው ይገባል ሲሉ ያቀረቡትን ጥያቄም በዝርዝር አስቀምጠዋል።

ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከልም የፌደራል መንግስቱ አስቸኳይ ለሆኑ የሰብአዊ ችግሮች በጀቱን እንዲጠቀም፣ በርካታ ድሃ ተኮር የሆኑ ፖሊሲዎችን እንዲያወጣ፣ በእርዳታ አቅርቦቱ ዙሪያ ተከታታይነት ያለው ሪፖርት እንዲያቀርብ የሚሉት ይገኝበታል።

በተጨማሪም የሰብአዊ ረድኤቱን ተግባር የሚያስተጓጉሉ ቢሮክራሲዎችን እንዲያስተካክል፣ የንጹሃንን እና የእርዳታ ሰራተኞች ደህንነት እንዲያስጠብቅ፣ ተፈናቃዮች በመላ ሀገሪቱ በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ማስቻል እና በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ወደ ቀያቸው የመመለስ ስራ እንዲያከናውን ጠይቀዋል። አስ

Exit mobile version