ዜናፖለቲካ

ዜና: ስልታዊ እና ተደጋጋሚ የዘፈቀደ እስራት ዘላቂ መፍትሔ ይሻል - የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13/2016 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ነጻነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች ላይ በተደጋጋሚ እና ስልታዊ በሆኑ መንገዶች የሚደርሱ የመብት ጥሰቶች ዘላቂ መፍትሔ ይሻል ሲል ዛሬ መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አሳሰበ።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ነጻነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች መብቶች ዙሪያ በአራት ክልሎች (በአማራ፣ ኦሮሚያ እና ሶማሊ ክልል፣ እንዲሁም በቀድሞው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል) ከሚያዝያ 2010 ዓ.ም. እስከ ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ባሉት አምስት ዓመታት ባከናወናቸው 4  ብሔራዊ ምርመራ /National Inquiry/ የተገኙ ዋና ዋና ግኝቶችን እና ምክረ ሐሳቦችን ያጠናቀረ ባለ 130 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል።

ኮሚሽኑ ከቃል ምስክርነቶች ባሻገር የሰነድ ማስረጃዎችን እና ምልከታዎችን በማከናወን ተጨማሪ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን አመላክቷል።

በዚሁም መሠረት ነጻነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች ላይ በተደጋጋሚ እና ስልታዊ በሆኑ መንገዶች የሚደርሱ የመብት ጥሰቶች መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች ማሰርን፣ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዝን፣ በፍርድ ቤት የተሰጠ የዋስትና መብትን በመጣስ ማሰርን ጨምሮ የዘፈቀደ እስራትን፣ ወሲባዊ ጥቃትን፣ ደብዛን አጥፍቶ ማሰርን፣ በግዳጅ መሰወርን፣ እና በቂ ምግብና ውሃ በሌላቸው፣ በተጨናነቁ፣ የንፅሕና እና የሕክምና አገልግሎት ባልተሟላላቸው እስር ቤቶች ማሰርን ጨምሮ ማሠቃየትን እና ያልተገባ አያያዝን፤ እንዲሁም በቤተሰብ፣ በሃይማኖት አማካሪዎች እና በሕግ አማካሪዎች የመጎብኘት መብትን መከልከልን ያካትታሉ።

ነጻነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች በማቆያ ቤቶች እና በማረሚያ ቤቶች ረዘም ላለ ጊዜ ከመቆየታቸው አንጻር የመተዳደሪያ ገቢያቸውን የሚያጡ መሆናቸው እንዲሁም ለጥሰቶቹ የመፍትሔ እና የካሳ ሥርዓት አለመኖሩ በእነዚሁ ብሔራዊ ምርመራ መድረኮች የተለዩ ተጨማሪ ክፍተቶች ናቸው ብሏል።

አንዳንድ ጥሰቶች እና ችግሮች ስልታዊ ከመሆናቸውም ባሻገር በብዙ ሰዎች ላይ በተደጋጋሚ የመፈጸም አዝማሚያን ያሳያሉ ሲል ገልጿል።

አብዛኛዎቹ የመብት ጥሰቶች የተፈጸሙባቸው ዐውዶች ከግጭት፣ ካልተመጣጠነ የመንግሥት የኃይል እርምጃ፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሁኔታዎች፣ ከምርጫ እንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ ሁኔታዎች ጋር የተያያዙ መሆናቸውን እና ጥሰቶቹን በመፈጸም ረገድ ሚሊሻዎች፣ የቀበሌ አስተዳዳሪዎች፣ የመደበኛ እንዲሁም የልዩ ኃይል ፖሊስ፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላት ተሳትፎ የነበራቸው መሆኑን በሕዝባዊ መድረኮቹ ከተለዩ ጉዳዮች መካከል እንደሚገኙበት አስታውቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ነጻነታቸውን ያጡ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች አስተማማኝ ጥበቃ የሚያገኙበትን፣ በአጥፊዎች ላይ ተጠያቂነት የሚረጋገጥበትን እንዲሁም ተጎጂዎች ካሳ የሚያገኙበትን ሥርዓት ለመዘርጋት የሕግ፣ የአስተዳደር፣ የፍትሕ፣ የፋይናንስ እና ሌሎች እርምጃዎችን መውሰድ የሚገባ መሆኑም በሪፖርቱ ተመላክቷል።

የብሔራዊ ምርመራውን ግኝቶች ተመሥርቶ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት ስልታዊ እና ተደጋጋሚ የዘፈቀደ እስራትን እና ተያያዥ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለማስቆም እንዲሁም መንስኤዎቻቸውን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲሠሩ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።

የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ነጻነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለማስቆም፣ በጥሰቶች ተሳታፊ የሆኑ አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ እና ለተጎጂዎች ተገቢ የሆነውን የካሳ ሥርዓት ለመዘርጋት ቁርጠኛ ሊሆኑ ይገባል ብሏል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button