ፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: “በምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮችን ለመመለስ በፌደራል መንግስቱ በኩል ምንም አይነት እንቅስቃሴ እየተደረገ አይደለም” - ጀነራል ታደሰ ወረደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12/2016 ዓ.ም፡- የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው ለመመለስ ዝግጅቱን ቢጨርስም ከፌደራል መንግስቱ በኩል ምንም አይነት እንቅስቃሴ እየተደረገ አይደለም ሲሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተናንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ገለጹ።

በደቡብ ራያ አከባቢ ከፌደራል መንግስቱ በኩል ግን መዘግየቶች የታያሉ ሲሉ የገለጹት ጀነራሉ “የመከላከያ ሀይሉ ስራውን ማዘግየት ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው እንዳንመልስ አድርጎናል” ብለዋል።

በደቡብ ራያ መፍረስ ያለበት አስተዳደር ፈርሷል፣ መውጣት የነበረበት ታጣቂም ወጥቷል ያሉት ሌተናንት ጀነራል ታደሰ ቀሪዎቹ ጉዳዮች በሰላማዊ መንገድ እንዲያልቁ ማድረግ ነው፣ ይህ የሚሆንበትን መንገድም እናመቻቻለን” ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተናንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ትላንት ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ.ም ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ “በምዕራብ ትግራይ (በመንግስት በኩል) ምንም አይነት የሚታይ እንቅስቃሴ የለም፣ ነገር ግን ምንም እንቅስቃሴ አልተደረገም በሚል ቀጣዩ ክረምት እንዲያልፍ አንፈቅድም፣ የዚህም ተባባሪያቸው አንሆንም” ሲሉ ገልጸዋል።

በተመሳሳይም “ወደ ግጭት እንድንገባ ለሚገፋፉንም አንተባበርም ወደ ግጭትም አንገባም” ያሉት ሌተናንት ጀነራል ታደሰ “ከፌደራል መንግስቱ እና ከፌደራል መንግስቱ የጸጥታ ሀይሎች በኩል የምንጠብቀው አለ፤ በእኛ በኩል የሚጠበቅብንን ትብብር እናደርጋለን፣ እነሱን ሊያስቸግር የሚችል ነገር አናደርግም” ብለዋል።

ተፈናቃዮች ሲመለሱ ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን እንሰራለን ሲሉ የተደመጡት ጀነራሉ መከላከያ ሀይሉ ይህንን ለመፈጸም የሚያስቸግረው ነገር ካለ ለመነጋገር ዝግጁ ነን ሲሉ አስታውቀዋል።

“ተፈናቃይ ወገኖቻችን ሲመለሱ ያላቸውን ይዘው እንዲመለሱ ይደረጋል” ሲሉ ገልጸው “ምንም አይነት ተኩስ እና ግጭት ያጋጥማቸዋል ብለን አንጠብቅም” ሲሉ ተናግረዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የፌደራል የጸጥታ ሀይሉ “ለመተግበር የሚያስቸግራቸው ነገር ካለ ለመነጋገር ዝግጁዎች ነን ያሉት ሌተናንት ጀነራል ታደሰ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ከዚህ በኋላ እንደተፈናቀሉ ለማቆየት የምናደርገው ምንም አይነት ነገር የለም ብለዋል።

በደቡብ ራያ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመመለስ “እኛ ዝግጅታችንን ጨርሰናል” ሲሉ የተደመጡት ጀነራሉ “ከዚህ መኋላ የሚኖረው ዝግጅት በመከላከያ የሚፈጸም ነው፤ እኛ ባስቀመጥነው የግዜ ሰሌዳ እንሄዳለን” ብለዋል።

“በራያ አከባቢ የሚጠበቅብንን ሃላፊነት እናውቃለን እናሟላለን፣ ሃላፊነታችንን እስከተወጣን ድረስ መመለስ ያለብንን ተፈናቃይ እንመልሳለን” ሲሉ ገልጸዋል።

“ተፈናቃዮቹን ወደ ቀያቸው የምንመልሰው በተቀመጠው የግዜ ሰሌዳ አማካኝነት ነው፤ በማንኛውም አጋጣሚ ግጭት የመፍጠር ፍላጎት የለንም፣ በዋናነት መከላከል የጋራ አላማችን ስለሆነ ከፌደራል መንግስቱ የጸጥታ ሀይል ጋር ወደ ግጭት ሊያስገባን የሚችል ምንም ነገር የለም” ሲሉ ተናግረዋል።

በጸለምት አከባቢም ተፈናቃዮች እንዲመለሱ ይደረጋል ያሉት ሌተናንት ጀነራሉ ታጥቆ ከቀየው የተፈናቀለም ከነትጥቁ ይመለሳል ሲሉ አስታውቀዋል።

“በህገወጥ መንገድ እዚያ አከባቢ መሬቱን በማረስ ላይ ያሉም ቁጥራቸው ስንት እንደሆነ እውቀዋለን” ሲሉ የተደመጡት ሌተናንት ጀነራሉ “በፊትም ቢሆን ከነትጥቁ እዚያ አከባቢ የሚኖረውንም ቢሆን እናውቀዋለን፤ የማምታታት ስራም አይኖርም፤ ከዚህም አዲስ አስታጥቀን የምናስገባው አይኖርም” ሲሉ ገልጸዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button