ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: “በፕሪቶርያው ስምምነት መሠረት የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ መፍታት አለባቸው” - የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16/2016 ዓ.ም፡- የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ዛሬ ሚያዚያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነቱ እስካሁን የተገኘው ውጤት እና እፎይታ እንደተጠበቀ ሆኖ ቀሪ ሥራዎችም አሉ ሲል ጠቁሞ በተለይ በስምምነቱ መሠረት የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ መፍታት አለባቸው ሲል ጠይቋል።

በፕሪቶሪያ ስምምነት እንደተገለጸው፣ በሕገ መንግሥታችንም እንደተደነገገው፣ እንደ ሀገር የሚኖረን አንድ የመከላከያ ሠራዊት ብቻ ነው ያለው መግለጫው ክልሎች በክልል ደረጃ ሕግ ለማስከበር ከሚያስፈልጋቸው ፖሊስ እና ሚሊሺያ ያለፈ የታጠቀ እና የተደራጀ ሠራዊት ሊኖራቸው አይችልም፤ አይገባምም ብሏል፤ በዚህ መሠረት ትጥቅ መፍታት እና ተያያዥ ሂደቶች በተሐድሶ ኮሚሽኑ ዕቅድ መሠረት በፍጥነት ሊተገበሩ ይገባል ሲል አሳስቧል።

በቤነሻንጉል ጉሙዝ፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በዐሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች እጃቸውን ሰጥተዋል ሲል ጠቅሷል።

በወቅታዊ ሀገራዊ የደህንነትና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱ ዛሬ ሚያዚያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ሁሉን አካታች ሀገራዊ ምክክር፣ የሽግግር ፍትሕ እና የተሐድሶ ተግባራትን በማከናወን “ዘላቂ ሰላምና ዘላቂ ብልጽግና ለማምጣት አዲስ የፖለቲካ ባህል” ያስፈልገናል ሲል አሳስቧል።

የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን የመጣው በጉልበት አይደለም ሲል ገልጾ ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር ብቻውን ግብ አይደለም ብሏል።

የኢትዮጵያ ችግር የአሁኑን አካሄድ በማስተካከል ብቻ አይፈታም ያለው መግለጫው በታሪክ ውስጥ የወረስናቸውን ስብራቶች መጠገንም የግድ ይለናል ሲል አሳስቧል።

እነዚህን የታሪክ ስብራቶች ለመጠገን ሦስት ዓይነት መፍትሔዎች በመንግስት መቀመጣቸውን ያመላከተው ምክር ቤቱ ነባሩን ፖለቲካዊ ችግር በሀገራዊ ምክክር መፍታት፤ የቅርብ ዘመናችንን የፖለቲካ ችግር ደግሞ በሽግግር ፍትሕ እና በተሐድሶ ማረም የሚሉት መሆናቸውን ጠቁሟል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በአሁኑ ወቅት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በነደፈው አካሄድ መሠረት በ10 ክልሎች እና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች ከየወረዳው በምክክሩ ሂደት የሚሳተፉ ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራ አጠናቋል። ከ679 ወረዳዎች፣ እስካሁን 12,294 ተሳታፊዎች ተለይተዋል።

በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ኮሚሽኑ በክልል ደረጃ የሚደረጉ የምክክር መድረኮችን ማካሄድ እንደሚጀምር ይጠበቃል። እንዲሁም የተሳታፊ ልየታ ባልተደረገባቸው ሁለት ክልሎች ላይ የተሳታፊዎች ልየታ በቅርቡ ይጠናቀቃል። በጉጉት የሚጠበቀው አካታች ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚካሄድ ተስፋ ይደረጋል።

ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ የሽግግር ፍትሕ በተመለከተ በኢትዮጵያ የበዳይ ተበዳይ አዙሪት ለመስበር የሽግግር ፍትሕ አንዱ ተመራጭ ስልት ነው ሲል ጠቁሞ ስለዚህም የሽግግር ፍትሕ ሂደት የሚመራበት የፖሊሲ ማሕቀፍ ጸድቋል ብሏል።

በሀገራችን ከመንግሥት ውጭ የሚኖር የታጠቀን ኃይል ሕገ መንግሥታችን አይፈቅድም ያለው የምክር ቤቱ መግለጫ ሰላማችንን የጸና ለማድረግ፣ እነዚህ የታጠቁ ኃይሎች ትጥቅ ፈትተው፣ የተሐድሶ ሂደት ውስጥ መቀላቀል አለባቸው ሲል አሳስቧል።

እነዚህ ሀይሎች የፖለቲካ ጥያቄዎቻቸውንም በሀገራዊ ምክክር ሂደት በመሳተፍ መፍታት ይችላሉ ሲል ያስታወቀው መግለጫው ለዚህ የሚሆን የተሐድሶ ኮሚሽን መቋቋሙን እና ዓላማውም መሣሪያ ማስፈታት፣ የትጥቅ ቡድኖችን ሰላማዊ ማድረግና ከማኅበረሰቡ ጋር መቀላቀል መሆናቸውነ አመላክቷል።

መንግሥትም የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አተገባበርን ከሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ጋር የተናበበ እና የሚመጋገብ እንዲሆን በማድረግ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ጠቁሟል።

ነባር ሀገራዊ ችግሮቻችንን በሀገራዊ ምክከር እና በሽግግር ፍትሕ እያረምን የገጠሙን የግጭትና የጦርነት ፈተናዎች ለመሻገር ደግሞ ሰላማዊ የፖለቲካ አካሄዶችን ተመራጭ ማድረግ አለብን ሲል አሳስቧል።

በመግለጫው ሌላ ክፍል በኦሮሚያ ክልልም በአንዳንድ የክልሉ ዞኖች የነበረው የታጣቂ ኃይሎች ሰፊ እንቅስቃሴ እና አንዳንድ ወረዳዎችን የመቆጣጠር አዝማሚያ ተቀልብሷል ሲል ገልጿል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም የጸጥታና የደኅንነት ሁኔታው በእጅጉ ተሻሽሏል ያለው መግለጫው በአዲስ አበባ እና በሌሎችም የሀገሪቱ ትላልቅ ከተማዎች የተለያዩ የሽብር ጥቃቶችን ለመፈጸም አቅደው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ዕቅድ ለማክሸፍም ተችሏል ብሏል።

የተሠራው ሥራ ወሳኝ ቢሆንም በቂ ግን አይደለም፤ ፖለቲካ ቅብ የሆኑ የተደራጁ የዝርፊያ እና የወንጀል ቡድኖችን በሚገባ መቆጣጠር ይገባናል ሲል አሳስቧል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button