ቢዝነስ

ዜና: የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ700 ሚሊየን ዶላር በላይ ብድር እንዲያጸድቅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7/2016 ዓ.ም፡- የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

ምክር ቤቱ በቅድሚያ ተወያይቶ ውሳኔ ያሳለፈው ከ700 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚሆን ከአራት የፋይናንስ ተቋማት የተገኘ የብድር ስምምነቶች ላይ መሆኑን ከጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ለምስራቅ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ግሪድ ማጠናከሪያ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ ከአፍሪካ የልማት ባንክ የተገኘ የ52 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር፣ ለስራ ፈጠራ እና የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል ከጣልያን መንግስት የተገኘ 10 ሚሊዮን ዩሮ፣ ለቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ ከዓለም ዐቀፍ የልማት ማህበር የተገኘ 255 ሚሊዮን ዶላር አንዲሁም ለፓወር ሴክተር ሪፎርም፣ ኢንቨስትመንትና ሞደርናዜሽን ፕሮጀክት ምዕራፍ አንድ ማስፈፀሚያ የሚውል 393 ሚሊዮን ዶላር ከዓለም ዐቀፍ የልማት ማህበር የተደረጉ የብድር ስምምነቶች መሆናቸውን መረጃው ያሳያል።

ከአፍሪካ የልማት ባንክ የተገኘው ብድር 0.01% ወለድ እና ብድሩን በማስተዳደር ረገድ ለሚወጡ ወጭዎች 0.1% የአገልግሎት ክፍያ የሚታሰብበት ሆኖ የ15 ዓመታት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ40 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ መሆኑን አስታውቋል።

ከጣልያን መንግስት የተገኘው ብድር ከወለድ ነጻ ከመሆኑም በላይ የ16 ዓመት የችሮታ ጊዜ ያለውና በ30 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ መሆኑን ጠቁሟል።

ከዓለም ዐቀፍ የልማት ማህበር የተገኙት ብድሮች ወለድ የማይታሰብባቸው፣ ብድሮቹን በማስተዳደር ረገድ ለሚወጡ ወጪዎች 0.75% የአገልግሎት ክፍያ ብቻ የሚታሰብባቸው፣ የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜ ያላቸው እና በ38 ዓመት ተከፍለው የሚጠናቀቁ መሆናቸውን አመላክቷል።

ምክር ቤቱ ሁሉም ብድሮች ከሀገራችን የብድር አስተዳደር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን በማረጋገጥ በሙሉ ድምጽ ተቀብሎ ረቂቅ አዋጆቹ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ ያሳያል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ባቀረባቸው 3 ረቂቅ አዋጆች እና 1 ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡

ሶስተኛው ምክር ቤቱ የተወያየው የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ ረቂቅ አዋጅ ሲሆን የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ስርዓትን በማሻሻል አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ፣ ተደራሽ፣ ግልጽና ውጤታማ ማድረግ፣ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መሰረታዊ የዜጎችን መብትና ነፃነት ለማክበርና ለማስከበር ሁሉን አቀፍ የምዝገባ ስርዓት መዘርጋት የሚገባ በመሆኑ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡

አራተኛው ምክር ቤቱ የተወያየበት ጉዳይ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚያስከፍለውን ክፍያ ለመወሰን በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ መሆኑን ጠቁሟል።

በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያያው በውጭ ጉዳይ ሚኒስተር በቀረቡ ሁለት የሁለትዮሽ ስምምነቶች ላይ ሲሆን  የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እና የሩሲያ መንግስታት መካከል ያለውን የአየር አገልግሎት ስምምነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተፈረመ ስምምነት ነው፡፡

ሌላው ስምምነት በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዥያ መንግሥታት መካከል የዲፕሎማቲክ እና ሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛን ለማስቀረት የተደረገ ስምምነት ነው፡፡

ምክር ቤቱም አዋጆቹን በሙሉ ድምጽ አጽድቆ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button