ዜናቢዝነስ

ዜና፡ በአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከሚተከሉ 29 ተርባይኖች መካከል የሶስቱ ተከላ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29/2016 ዓ.ም፡- በ145 ሚሊዮን ዩሮ በጀት በመገንባት ላይ በሚገኘው የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከሚተከሉ 29 ተርባይኖች መካከል የሦስቱ ተከላ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አስታወቀ።

100 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እያንዳንዳቸው 3 ነጥብ 465 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው 29 ተርባይኖች አሉት ሲሉ የፕሮጀክቱ የሳይት ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ አብርሃም መግለጻቸውን ከኤሌክትሪክ ሀይሉ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

50 በመቶ የሚሆኑት የንፋስ ተርባይንና የጀነሬተር አካላት እንዲሁም 99 በመቶ ለማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ የሚያስፈልጉ ዕቃዎች ሳይት መድረሳቸውን መግለጻቸውን አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ የሲቪል ሥራ 48 ነጥብ 5 በመቶ እንዲሁም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራው 4 ነጥብ 9 በመቶ መጠናቀቁን እና አጠቃላይ አፈፃፀሙ ደግሞ 50 በመቶ ላይ መድረሱን ሃላፊው መግለጻቸውን መረጃው አመላክቷል።

የ12 የንፋስ ተርባይን ማማ መትከያ የመሰረት ሥራዎች የኮንክሪት ሙሌት ሲጠናቀቅ የሦስቱ የብረት ሥራ ተጠናቆ ለኮንክሪት ሙሊት ዝግጁ ነው ሲሉ የፕሮጀክቱ የሲቪል ሥራዎች ተቆጣጣሪ አቶ ደረጄ ጣሰው መናገራቸውን አስታወቋል።

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሂጦሳ ወረዳ በኢተያ ከተማ አካባቢ እየተገነባ የሚገኘው የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ሀገሪቱ ከንፋስ የምታገኘውን የኤሌክትሪክ ኃል ወደ 544 ሜጋ ዋት እንደሚያሳድገው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል በይፋዊ የፌስቡክ የማህበራዊ ትስስር ገጹ ያጋራው መረጃ ያሳያል።

የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የግንባታ ሥራ ሲመንስ ጋሜሳ በተሰኘ ኩባንያ በመከናወን ላይ መሆኑን እና ለግንባታው 145 ሚሊዮን ዩሮ በጀት እንደተያዘለት ጠቁሟል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button