ዕለታዊፍሬዜናማህበራዊ ጉዳይ
በመታየት ላይ ያለ

ዕለታዊ ዜና፡ የህዳሴ ግድብን ማዕከል ያደረገ አዲስ ከተማ ሊመሠረት መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28/ 2016 ዓ.ም፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ማዕከል ያደረገ አዲስ ከተማ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ሊመሠረት መሆኑን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ኢንጂነር) ገለፁ፡፡

ሚኒስትሩ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የታቀደው የህዳሴ ግድብ ከተማ መመሥረት ለህዳሴ ግድቡ ከለላና ጥበቃ እንደሚሆን እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚታየው ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት የሚተነፍስበት ይሆናል ሲሉ መግለፃቸውን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡

“ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡ የሚፈጥረው ዕድል አዲስ ከተማ እንዲመሠረት የሚያስገድድ ነው” ያሉት ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ኢንጂነር)፣ ለሚመሠረተው አዲስና ዘመናዊ ከተማ የሀብት ምንጭ የሚሆነው ከግድቡ ጀርባ በሚታቆረው ውኃ መሆኑን አስረድተዋል።

“የግድቡ ውኃ የሚፈጥረው የቱሪዝም መዳረሻነትና በውስጡ የሚፈጠሩት ደሴቶች፣ አምስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የኮርቻ ግድብ የሚፈጥረው ምቹ ዕይታና መስዕብ፣ የዓሳ ሀብትና የዓሳ ምርትን የማቀነባበር ሥራ የመሳሰሉት ከተሜነት እንዲፈጠር ያስገድዳሉ። ስለዚህ ይህንን ዕድል መጠቀም የግድ ነው” ብለዋል፡፡

በግድቡ አካባቢ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት ምቹ መሆኑን የገለፁት ኢንጂነር ሀብታሙ በሚፈጠረው ከተማ ማንኛውም ዜጋ ለመኖር ቢያስብ እንዲሁም ዜጎች ቦታውን እንደ ከተማ በመመልከት በከተሜነት ቢኖሩ ሕይወታቸውን በማሻሻል ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚችሉ ተናግረዋል ሲል የዜና አውታሩ ዘግቧል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button