ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: የህዳሴ ግድብ ቀሪ ስራዎችን ለማጠናቀቅ 50 ቢሊየን ብር ያስፈልጋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25/2016 ዓ.ም፡- የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አጠቃላይ የፋይናንስ ወጪ 191 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር መድረሱን እና ቀሪ የግድቡን የግንባታ ሥራዎች ለማጠናቀቅም 50 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ አስታወቁ።

ስራ አስኪያጁ ይህንን ያስታወቁት “በህብረት ችለናል” በሚል መሪ ቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን 13ኛ ዓመት አስመልክቶ በአዲስ አበባ በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ባጋራው መረጃ ገልጿል።

የኮንትራት ማሻሻያ መደረጉ፣ የተጣበበ የፕሮጀክት ጊዜ ሰሌዳና በግንባታ ወቅት በግድቡ መሠረት ላይ ያጋጠመ ልል ድንጋይ መኖሩ እንዲሁም የልምድ ማነስ እና የጥራትና ልኬት በሚፈለገው ደረጃ አለመሆን በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

በግድቡ ግንባታ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታትም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የቦርድ አመራር እስከ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ድረስ የመዋቅር ለውጥ ተደርጓል ያሉት ሥራ አስኪያጁ በዘርፉ ልምድ ያላቸውን ሥራ ተቋራጮች ከመቅጠር ጀምሮ በቂ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲመቻች መደረጉንም ተናግረዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ህግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀኔራል አምባሳደር ረታ አለሙ እንደገለፁት የፕሮጀክቱን ግንባታ ከማፋጠን በተጓዳኝ ግድቡ የህልውና ጉዳይ መሆኑን የሚሳይ የዲፕሎማሲ ስራ እየተሰራ ነው።

የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የኮንክሪት ሙሌት ግንባታ 99 ነጥብ 2 በመቶ መድረሱን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ በውይይቱ ወቅት መናገራቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ከ10 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የኮንክሪት ሙሌት ውስጥ የ10 ነጥብ 65 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ሙሌት ተጠናቋል ሲሉ የተናገሩት ስራ አስኪያጁ በአሁኑ ወቅት የግድቡ የሲቪል ሥራዎች 99 ነጥብ 2 በመቶ እንዲሁም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች አፈፃፀም 79 በመቶ መድረሱንም ጠቁመዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

እንደ ኢንጂነር ክፍሌ ገለፃ የውሃ ማስተላለፊያና መቆጣጠሪያ የብረታብረት ሥራዎች አጠቃላይ አፈፃፀም 90 በመቶ ተከናውኗል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button