ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን አል-ሸባብ እየተንቀሳቀሰ ነው ፤ የጸጥታ ስጋት ፈጥሯል በማሉን የአካባቢው ባለስልጣናት አስተባበሉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23/2016 ዓ/ም፡- በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን አልሻባብ እየተንቀሳቀሰ ነው፤ በርካታ የዞኑን ፖሊስ አባላትና ሚሊሻዎችን ገድሏል መባሉን የአካባቢው ባለስልጣናት አስተባበሉ።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም ይፋ ባደረገው ባለ 130 ገጽ ብሔራዊ ምርመራ ሪፖርት፤ “በባሌ ዞን ደን ውስጥ፤ የውጭ ዜጎች በሆኑና በኬንያ፣ ሶማሊያ እና ኡጋንዳ በሠለጠኑ ሰዎች የአል-ሸባብ የሽብር ቡድን መመስረቱ” በዞኑ የፀጥታ ስጋት መሆኑን አስታውቋል። 

ነጻነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች መብቶች ዙሪያ በአራት ክልሎች ከሚያዝያ 2010 ዓ.ም. እስከ ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ያካተተው የብሔራዊ ምርመራው ሪፖርት፤ የባሌ ዞን ፖሊስ ሃላፊ ረዳት ከሚሽነር ጀይላን አማንን ዋቢ በማድረግ “ቡድኑ አባላት መመልመሉን እና ስልጠና መስጠቱን” አስታወቋል። በማከልም፤ በርካታ የዞኑ ፖሊስ አባላት እና ሚሊሻዎች በአልሸባብ ቡድን መገደላቸውን እንዲሁም ፖሊስ መልሶ እርመጃ መውሰዱን” ገልጸዋል።

ነገር ግን ረዳት ኮሚሽነር ጀይላን አማን ለአዲስ ስታንዳርድ በባሌ ዞን የሚንቀሳቀስ የአልሸባብ ቡድን አለመኖሩን ገልጸዋል። በአካባቢው በቡድኑ የተገደሉ ሲቪሎችም ሆኑ የፀጥታ ኃይል አባላት እንደሌሉ በመግለጽ ስለ ኢሰመኮ ሪፖርት እንደማያውቁም ተናግረዋል። 

የአጎራባች ምስራቅ ባሌ ዞን የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ናታ ዳባ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት፤ በጥቅምት 2016 አራት የአልሸባብ አባላት ተይዘው ለመከላከያ ሰራዊት ተላልፈዋል፤ አንደኛው ደግሞ ተገድሏል።

በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልል ድንበር አካባቢ በተለይም በምስራቅ ባሌ ዞን ራይቱ ወረዳ የአልሸባብ ቡድኖች ይንቀሳቀሳሉ ቢባልም “እስካሁን  በአካባቢው በተደረገ ቁጥጥር የአልሸባብ ሽብር ቡድን አላገኘንም፤ የሉም” ብለዋል። በተጨማሪም በምስራቅ ባሌ ዞን በቡድኑ የተገደለ ሰው አለመኖሩን እና ቡድኑ የፀጥታ ስጋት እንደማይፈጥር ተናግረዋል።

በምስራቅ ባሌ ዞን የሚገኙ አምስት ወረዳዎች ማለትም ሳዌና፣ ራይቱ፣ ለገ ሂዳ፣ ዳዌ ቀጫን እና ዳዌ ሰረር፤ ከሶማሊያ ክልል ጋር የሚዋሰኑ ሲሆን ሶማሌ ክልል ደግሞ አል-ሸባብ የተባለው ታጣቂ ቡድን የሚገኝበት ከሶማሊያ ጋር ይዋሰናል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button