ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ አደራዳሪዎች በተገኙበት በፕሪቶርያው ስምምነት ዙሪያ በቀጣይ ሳምንታት የፌደራል መንግስቱ እና ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይወያያሉ ተባለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20/2016 ዓ.ም፡- የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ የካቲት 18 እና 19 ቀን 2016 ዓ.ም መሰብሰቡን እና የተለያዩ ውሳኔዎች ማሳለፉን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ረዳኢ ሀለፎም ከትግራይ ቴሊቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።

ካቢኔው ባካሄደው ስብሰባ የአስተዳደሩን ስራዎች ለመስራት አስቸጋሪ የነበሩ መመሪያዎችን ማሻሻሉን ጠቁመዋል።

በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ዙሪያ አደራዳሪ አካላት በተገኙበት የፌደራል መንግስት እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል በቀጣይ ሳምንታት ውይይት እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።

የፕሪቶርያው ስምምነት አለመተግበሩ የክልሉ ህዝብ ላይ የሚደርሰው መከራና ስቃይ ሊቆም አልቻለም ሲሉ የገለጹት ሃላፊው የትግራይ ክልል ግዜያዊ አስተዳደር ከፌደራል መንግስቱ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በስምምነቱ አፈጻጸም ዙሪያ በተደጋጋሚ መምከሩን ገልጸዋል።

በሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ እና ፖለቲካዊ መንገድ የትግራይን ህዝብ ጥያቄ እንዲመለስ ማድረግ ዋነኛ ተመራጭ መንገድ ነው ሲሉ እምነታቸውን ኣጋርተዋል።

የአፍሪካ ህብረት፣ የመንግስታቱ ድርጅት፣ የአሜሪካን እና የደቡብ አፍሪካ መንግስታት ተወካዮች ተሳታፊ የሚሆኑበት የፕሪቶርያውን ውል አፈጻጸም የተመለከተ ውይይት ለማካሄድ ቀጠሮ መያዙን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የካቲት 5 ቀን 2016 ቀን ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መናገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በረሃብ ምክንያት የሚሞቱ የክልሉ ነዋሪዎችን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ በረሃብ ምክንያት የሚከሰተውን ሞት ለማስቀረት የሚያስችል መፍትሔ ለማስገኘት ከፌደራል መንግስቱ ጋር የነበሩ ልዩነቶችን መፍታት መቻሉን ጠቁመው በአንድ ማዕቀፍ መፍትሔ ለማበጀት እየተጣረ መሆኑን አመላክተዋል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button