ዜናፖለቲካ

ዜና፡ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ሥራዎችን ለመሥራት መዘጋጀቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19/2016 ዓ.ም፡- ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ሥራዎችን ለመሥራት የተሟላ ዝግጅት እንዳለው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

የጸጥታ ችግሮች ባሉባቸው አካባቢዎችም ከመንግሥት፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ከሲቪክ ማኅበራት ጋር በመተባበር ኮሚሽኑ በመስራት ላይ እንደሚገኝ የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር ዮናስ ገልጸውልኛል ያለው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በተለይ መከላከያ ሠራዊቱና ፖሊስ ሽፋን በመስጠታቸው ሥራዎች በመሠራት ላይ ናቸው ማለታቸውን አመላክቷል።

በቅድመ ዝግጅቱ ወቅት በአማራ ክልል ባሉ አካባቢዎች የተሳታፊ ልየታ ለማድረግ በታሰበበት ወቅት ግጭት ተፈጥሮ እንደነበረ ያወሱት ዶ/ር ዮናስ ኮሚሽኑ ተስፋ ሳይቆርጥ ከክልሉ አመራሮች፣ ከሲቪክ ማኅበራት፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎችና ከምሁራን ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ገልጸዋል ብሏል።

በሌሎች አካባቢዎች የተጀመሩትን ሥራዎች ግጭቱ ባለባቸው አካባቢዎችም ጎን ለጎን ለማስኬድ በኮሚሽኑ በኩል የተሟላ ዝግጁነት መኖሩን አስታውቀዋል ሲል ዘገባው አካቷል።

ከአማራና ትግራይ ክልል ውጪ በክልሎች እና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የእስካሁኑን ሥራዎች በሚገባ አጠናቅቀናል» ሲሉ ተናግረዋል ያለው ዘገባው የተሳታፊ ልየታን በሚመለከት በሲዳማ ክልል፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሐረሪ እና በሱማሌ ክልሎች እየተጠናቀቀ ነው ማለታቸውን አመላክቷል።

የእስካሁኑ ሥራ ከ90 በመቶ በላይ ክልሎች ላይ ተጠናቅቋል፣ በኦሮሚያ ክልልም ቢሆን በስፋት እየተሠራ ይገኛል፣ በቅርቡ ይጠናቀቃል ማለታቸውንም አካቷል።

በትግራይ ክልልም ምሁራንን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ጠቅሰው፤ በሁሉም በኩል ምክክር ለማካሄድ አዎንታዊ ፍላጎትና አመለካከት እንዳለ ተናግረዋል ያለው ዘገባው ችግሮችን ለመፍታት እየተነጋገሩ ነገሮች ሲስተካከሉ ኮሚሽኑ ወደ ምክክር እንደሚገባ ተስፋ ተሰጥቷል ማለታቸውን አስታውቋል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button