አዲስ አበባ፣ መስከረም 22/2016 ዓ.ም፡– የኢትዮጵያን ጨምሮ ካርቱም በሚገኙ የበርካታ ሀገራት ኤምባሲ ላይ በዛሬው ዕለት መስከረም 22 ቀን 2016 ዓ.ም ጠዋት ላይ የከባድ መሣሪያ ጥቃት መፈጸሙን ቢቢሲ ዲፕሎማቲክ ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ አስታውቋል።
ከኢትዮጵያ ኤምባሲ በተጨማሪ በዩናይትድ አረብ ኤምሬት፣ በሩሲያ እና በደቡብ አፍሪካ ኤምባሲዎችም ላይ ጥቃት መፈጸሙን ጠቁሟል።
ሱዳን ካርቱም ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ በተፈጸመ የከባድ መሣሪያ ጥቃት በኤምባሲው ሕንጻ እና ንብረት ላይ ውድመት መድረሱን ያስታወቀው ቢቢሲ በሰው ላይ ግን ምንም ዓይነት ጉዳት አለመድረሱን የዲፕሎማሲ ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ አመላክቷል።
በካርቱም አል-አማራት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ባለፉት ወራት በተለያዩ ኃይሎች ተደጋጋሚ ጥቃት እና ዘረፋ እንዳጋጠመው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ዲፕሎማት ተናግረዋል ብሏል።
በጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል በኤክስ (ትዊተር) ገጹ ላይ ዛሬ ጠዋት በኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ ጥቃት መድረሱን መግለጹንም ዘገባው አካቷል። ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ለጥቃቱ ተቀናቃኙን በጄኔራል አብደል ፋታህ አልቡርሐን የሚመራውን የሱዳን ጦር ሠራዊትን ተጠያቂ ያደረገ ሲሆን፣ በኤምባሲው ላይ በተፈጸመው ጥቃት “በሕንጻው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል” ብሏል።
በኤምባሲው ላይ ጥቃቱ ለምን እንደተፈጸመ እስካሁን የታወቀ ነገር የሌለ ሲሆን፣ ስለክስተቱ በኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ በጄኔራል አልቡርሐን ኃይሎች በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም። አስ