የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን በአገር ውስጥ ማምረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16/2016 ዓ.ም፡- በርካታ የሀገሪቱ ባለስለጣናት በተገኙበት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን በአገር ውስጥ ማምረት በሚቻልበት ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተካሄደ።

ለውይይት የሚሆን የመነሻ ሰነድ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በረኦ ሀሰን አማካኝነት የቀረበ ሲሆን አሁናዊ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሁኔታ፣ በሀገር ውስጥ ለማምረት ያሉ ምቹ አጋጣሚዎች፣ ተግዳሮቶች እና የሚጠበቅ ውጤት በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን ቁጥር ለመጨመር ካሉት ምቹ አጋጣሚዎች ውስጥ በቂ የታዳሽ ሃይል መኖር፣ የፖሊሲ ድጋፍ፣ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት እና በሁሉም የመንግስት ተቋማት ቅጥር ግቢ የቻርጅ ማድረግያ መሰረተ ልማት ለማስፋፋት ምቹ መሠረተ ልማት መኖሩ የተመላከተ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአንጻሩ የቻርጅ መሙያ መሰረተ ልማት በሚፈለገው ደረጃ ያለመስፋፋት፣ በኤሌክትሪክ ተሸከርካሪ ላይ ያለው የግንዛቤ ክፍተት እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት በተግዳሮትነት ተጠቅሰዋል።

ገለፃውን ተከትሎ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶ/ር አለሙ ስሜ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን በአገር ውስጥ እንዴት መገጣጠም እንደሚቻል፣ ከውጭ ለሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን በምን አግባብ መደገፍ እንደሚቻል እና የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትን በሚመለከት የውይይት ነጥቦችን አንሥተዋል።

በውይይቱ ወቅት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው በየማድያው የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪ ሀይል መሙያ እንዲኖር ማድረግ እና የሃይል መሙያ መሰረተ ልማት ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ ከሊዝ ነፃ መሬት ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት ከኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት አንጻር ለአሁኑ በቂ የሚባል የሃይል ክምችት መኖሩን እና ወደ አምስት የሚጠጉ ፕሮጄክቶች በግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተወካዮች አመላክተዋል፡፡

የውይይት መድረኩ ማጠቃለያ ዶ/ር አለሙ ስሜ የውይይቱ ዋና ዓላማ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን በአገር ውስጥ እንዴት ማምረት እንደሚቻል መነጋገር ቢሆንም እስከዚያው ድረስ አገር ውስጥ በከፊል እየተገጣጠሙ ያሉት እና ከውጭ የሚገቡትን የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን ማበረታታት እንደሚገባ መጠቆማቸውን ከትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል። አስ

Exit mobile version