ርዕሰ አንቀፅፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ርዕስ አንቀጽ: በአባይ የመልማት መብት ለኢትዮጵያ የሉዓላዊነት ጉዳይ ነዉ፣ የተፋሰሱ ሀገራት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሊረጋገጥ ይገባል!

አዲስ አበባ መስከረም 8/ 2017 ዓ/ም፦ በዓለማችን በርዝመቱ ተወዳዳሪ የሌለው የአባይ ወንዝ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራትን አቆራርጦ በመፍሰስ፣ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ከውሃ ምንጭነት ባለፈ ጉልበታቸው እና የህልውናቸው መሰረት ሆኖ ያገለግላል። ለዘመናት ወንዙ በሚያቋርጥባቸው አከባቢ የሚኖሩ ህዝቦች የተፈጥሮ ሀብቱን ተጋርተው ኑረዋል፤ የኑሯቸው ምንጭ የመሆኑን ያክል የውጥረታቸውም ምክንያት ሁኖ አገልግሏል። ምንም እንኳ የውጥረቱ መንስኤ የሚመነጨው ወንዙን እና የተፈጥሮ ሀብቱን በብቸኝነትና በቋሚነት በመቆጣጠር ለብቻዋ ተጠቃሚ መሆንን በምትፈልገው በግብጽ በኩል ቢሆንም።

ይህ የዘመናት የግብጽ ወንዙን በብቸኝነት የመጠቀም ፍላጎት የህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረተ ዲንጋይ ከ13 አመታት በፊት በወቅቱ የሀገሪቱ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከተበሰረበት የመጀመሪያው ቀን ጀምሮ አደባባይ ላይ ወጥቶ ተጋለጠ። ግብጽ መቀበል ያልፈለገችው ዋነኛው ጉዳይ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን እየገነባች ያለው ለመልማት እና ለብሔራዊ ኩራት ብቻ ሳይሆን ሉዓላዊ እና ቅቡል የሆነውን መብቷን እየተገበረች ስለመሆኑ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የወንዙን ውሃ በፍትሀዊነት የመጠቀምን መብት እውቅና መስጠት የማይሻው የግብፅ ግትር አቋም በወንዙ ላይ የ85 በመቶ ውሃ ምንጭ በሆነችውን ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ላይ የሚንጸባረቅ ነው። ይህ ግትር አቋም ሊቀየርበት የሚገባው ወሳኙ ግዜ አሁን ነው።

በፖለቲከኞች እና በውሃ ባለሙያዎች መካከል በተካሄደ የዓመታት አድካሚ ድርድር በኋላ በማያጨቃጭክ መልኩ ከመጡ የመፍትሔ ዘዴዎቸ መካከል የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (ሲኤፍኤ) አንዱ ነው። የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱ በተፋሰሱ ሀገራት ተንሰራፍቶ የቆየውን ስህተት ማረሚያ፣ ለዘመናት ሰፍኖ የቆየውን ኢፍትሓዊነት ማስተካከያ ወሳኝ መንገድ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባዋል።

ሆኖም ግን ይህንን ማዕቀፍ ከተጠነሰሰበት አስር አመታት በኋላም ቢሆን አልፈርምም፣ አላጸድቅም በሚል በጽኑ ተቃውሞዋን የገፋችበት ዋነኛ ሀገር ግብጽ ነች። ሁሉም የናይል ተፋሰስ ሀገራት ፍትሃዊ የውሃ አስተዳደርን ለማስፈን ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ቀጣናዊ መረጋጋት እና ቀጣይነት ያለው ልማት ለማረጋገጥ የትብብር ማዕቀፉ ተግባራዊ እንዲሆን በጋራ መቆም ይገባቸዋል።

ግብጽ መቀበል ያልፈለገችው ዋነኛው ጉዳይ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን እየገነባች ያለው ለመልማት እና ለብሔራዊ ኩራት ብቻ ሳይሆን ሉዓላዊ እና ቅቡል የሆነውን መብቷን እየተገበረች ስለመሆኑ ነው

ከታሪክ አኳያ የአባይ ወንዝ አስተዳደር በዋናነት የታችኛው የተፋሰሱን ሀገራት ግብጽና ሱዳንን ተጠቃሚ በሚያደርግ በቅኝ ግዛት ዘመን በተደረጉ ስምምነቶች የተቃኘ ነው፤ የተፋሰሱን የላይኛው ሀገራት በተለይም የወንዙን ውሃ 85 በመቶ የምታበረክተውን ኢትዮጵያን ህጋዊ ፍላጎት ችላ በማለት። እነዚህ የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶች የተፋሰሱን የላይኛው ሀገራት በመተው የወንዙን ​​ውሃ አብዘሃኛውን መጠን ለግብፅ እና ለሱዳን መድበው ያከፋፈሉ ናቸው፤ የላይኛው የተፋሰሱ ሀገራት በወንዙ ውሃ ላይ በከፍተኛ ደረጃ ለሚያበረክቱት አስተዋፅዖ እንኳ የይገባኛል ጥያቄ እንዳያቀርቡ በነፈገ መልኩ።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ የተቀረጸው የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱ ይህንን ሚዛን አልባ አጠቃቀም ለማረም በሚል ነበር፤ ምክንያታዊ አጠቃቀም፣ ዘላቂነት ያለው እና ትብብርን የሚያሰፍን፣ በመርህ ላይ የተመሰረተ፣ ፍትሃዊ የውሃ ክፍፍል ማዕቀፍ በማዘጋጀት ይህንን ሚዛን መዛባት ለማስተካከል ጥረት የሚያደርግ ነው።

ከምንም በላይ ግን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱ በወንዙ አጠቃቀም ዙሪያ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል የሚፈጠሩ ውጥረቶች ወደ ግጭት ከማምራታቸው በፊት የውይይት፣ የትብብር እና የግጭት መፍቻ ዘዴዎች እንዲቀርቡ ያመቻቻል።

እንደ የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ አገላለጽ ከሆነ የተፋሰሱ ስድስት ሀገራት ስምምነቱን ፈርመው ህግ እንዲሆን የሚያስችል ሰነድ ለአፍሪካ ህብረት በነሃሴ 8 ቀን 2016 ዓ.ም በማቅረባቸው ሳቢያ የትብብር ማዕቀፉ እውን የመሆን ሂደተ ተጠናቋል። ስምምነቱ ከጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል፣ ይህም የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን እንዲቋቋም ያስችላል። እስካሁን ስድስት ሀገሮች፡ ኢትዮጵያ፣ ብሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ሁሉም ማዕቀፉን አጽድቀዋል፣ ሰነዱን አስረክበዋ፤ ካለጸደቁት የተፋሰሱ ሀገራት መካከል እንደሚታወቀው ግብጽ እና ሱዳን ይገኙበታል።

የህዳሴ ግድብ እውን ሆኗል/የማይቀለበስ ደረጃ ላይ ይገኛል፤ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያሉዓላዊነት ጉዳይ መሆኑን ግብፅ መቀበል ይገባታል

በተለይም በግብፅ እና በሱዳን በኩል የትብብር ማዕቀፉን አለመፈረማቸው እና አለማጽደቃቸው ዲፕሎማሲያዊ እና አካባቢያዊ እንቅፋት ብቻ ሳይሆን ግብፅ በበላይነት ኢፍትሃዊ በሆነ መልኩ የናይል ውሃ አጠቃቀሟን እንድትቀጥልበት የሚያስችል መድረክ የሚፈጥር ነው። አሁንም ቢሆን ግብፅ ከሌሎቹ የናይል ተፋሰስ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ከማጠናከር እና በትብብር ማዕቀፍ በመካተት ፍትሃዊ እና ትብብርን ማዕከል ያደረገ መፍትሄ ላይ ከመስራት ይልቅ አሁንም መሰረተቢስ ክሷን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት (UNSC) አቅርባለች፤ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን በመገንባት የአባይን ውሃ የመጠቀም ህጋዊ መብቷ ላይ ስጋት እየደቀነች ትገኛለች።

የግብፅ የቅርብ ጊዜ እየወሰደችው ያለው እርምጃ በበርካታ ምክንያቶች የተሳሳተ ነው፤ ከሁሉም በላይ ግን ሁለት ምክንያቶች ጎልተው መቅረብ ይችላሉ። የመጀመሪያው የህዳሴ ግድብ እውን የሆነ/የማይቀለበስ ደረጃ ላይ ይገኛል፤ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የሉዓላዊነት ጉዳይ መሆኑን ግብፅ መቀበል ይገባታል።

ሁለተኛው አመክንዮ የአባይ ጉዳይ በመሰረታዊነት አህጉራዊ ጉዳይ ሁኖ እያለ ወደ መንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በመውሰዷ አለም አቀፍ ጉዳይ እንዲሆን ማድረጓ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አብዛኛዎቹ ለወንዙን ​​ውሃ አበርክቶ ያላቸው የተፋሰሱ ሀገራት ጉዳዩን እንደ አህጉራዊ ጉዳይ አድርገው በማየታቸው የአፍሪካን መፍትሄ የሚፈልግ አድርገው አቅርበውታል።

የህዝብ ቁጥር በፍጥነት እያደገ ባለበት እና የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት ባየለበት በአሁኑ ወቅት የናይል ተፋሰስ የወደፊት እጣ ፈንታ በትብብር ላይ የተመሰረተ ነው፤ዛቻ እና ዲፕሎማሲያዊ ማስፈራራት አይደለም

የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ጣልቃ ገብነትን በመሻቷ ግብፅ በተቀሩት የተፋሰስ ሀገራት የመገለልን አደጋ በራሷ ላይ ደቅናለች፤ የተፋሰሱ ሀገራት በከፍተኛ ተጋድሎ የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን መመስረት የሚያስችል ምዕራፍ እንዲከፈት አድርጋለች። ሁሉም የናይል ተፋሰስ አገሮች በአንድ ወጥ ማዕቀፍ ውስጥ ለመሰባሰብ ግዜ በፈጁ ቁጥር፣ ከውሃ እጥረት ጋር እና ከቀጠናዊ ውጥረት ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ በርካታ ችግሮችን በማወሳሰብ መፍትሔ ማፈላለግን አዳጋች እንዲሆን ያደርጋል።

የግብፅ የኢትዮጵያ ችግር ናት የሚለው የተሳሳተ ግንዛቤ ስህተት ነውና መቆም አለበት። የተቀሩት የተፋሰሱ ሀገራት የትብብር ማዕቀፉን እንዲፈርሙ እና እንዲያጸድቁ የቀጠናው መሪዎች እና አለም አቀፉ ማህበረሰብ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን በማጠናከር ግፊት ማደረግ ይጠበቅባቸዋል።

የህዝብ ቁጥር በፍጥነት እያደገ ባለበት እና የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት ባየለበት በአሁኑ ወቅት የናይል ተፋሰስ የወደፊት እጣ ፈንታ በትብብር ላይ የተመሰረተ ነው፤ በዛቻ እና ዲፕሎማሲያዊ ማስፈራራት አይደለም። የትብብር ማዕቀፉን መፈረም ፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት ብቻ ሳይሆን የተፋሰሱ ሀገራት የናይልን ወንዝ ፍትሃዊ በመሆነ መልኩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማስቻል የሞራል ግዴታ ነው። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button