ዜናፖለቲካ

ዜና: ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሰኔ 16 ቀን ‘‘ቀሪ’’ እና “ድጋሚ ምርጫ” በሚካሄድባቸው አከባቢዎች የምርጫ ሂደቶች የሰብአዊ መብቶች ክትትል አደርጋለሁ አለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27/2016 ዓ.ም፡-የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በ6ኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ወቅት ምርጫ ባልተካሄደባቸው እና ድጋሚ ምርጫ እንዲደረግባቸው ውሳኔ በተሰጠባቸው አከባቢዎች የሚካሄዱትን የምርጫ ሂደቶች የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሚያደርግ መሆኑን አስታውቋል።

ኢሰመኮ በተሻሻለው መቋቋምያ አዋጁ መሰረት በ2013 ዓ.ም. የተካሄደውን 6ኛውን ጠቅላላ ምርጫ እና በቀድሞው ደቡብ ክልል ጥር 29 ቀን 2015 እና ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. የተደረጉት ሕዝበ ውሳኔዎች የሰብአዊ መብቶች ክትትል በማድረግ ሪፖርቱን ይፋ ማድረጉን አስታውሷል።

የኢሰመኮ የምርጫ ወይም የሕዝበ ውሳኔ ወቅት የሰብአዊ መብቶች ክትትል በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅት እና በድኅረ ምርጫ ወቅት እንደሚያከናውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ክትትሉ በዋናነት በእነዚህ ሂደቶች ወቅት ተፈጻሚ ሊሆኑ የሚገባቸውን የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች እና መርሖችን መሠረት የሚያደርግ መሆኑን ጠቁሟል።

ከአራቱም ክልሎች በተመረጡ ከ200 በላይ የምርጫ ጣቢያዎች የሚሰማሩ የኢሰመኮ የክትትል ባለሞያዎች በምርጫ ወቅት ከሚያደርጉት የመስክ ምልከታ በተጨማሪ መራጮችን፣ የምርጫ አስፈጻሚዎችን፣ የፀጥታና የአስተዳደር አካላትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል እጩዎችን፣ ልዩ ልዩ ታዛቢዎችን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማነጋገር መረጃ እና ማስረጃ የሚሰበስቡ መሆኑን አስታውቋል።

የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ የሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን በምርጫው ሂደት የመሳተፍ መብት እንዲረጋገጥ አስፈላጊውን በማድረግ ረገድ እንዲሁም በሕግ የተደነገጉ የምርጫ ወቅት መመሪያዎችን በማክበር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ጥረት ሁሉ እንዲያደርጉ ኢሰመኮ ጥሪ አቅርቧል።

በምርጫ ወቅት የሚነሱ ማንኛውም ዓይነት አቤቱታዎች እና ክርክሮችን የምርጫ ሕጉንና ሌሎች አግባብነት ያላቸውን ሕጎች ባከበረ መልኩ እንዲፈቱ ሁሉም ባለድርሻዎች ጥረታቸውን እንዲያጠናክሩ የተቋሙ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል አሳስበዋል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button