ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: በአማራ ክልል እየተካሄደ ካለው ግጭት ጋር ተያይዞ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና ምሁራን እንዲፈቱ ተጠየቀ

የፌደራል መንግስት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊና ተፈፃሚ እንዲያደርግም ተጠይቋል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19/2016 ዓ.ም፡-በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና በክልሉ በሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረው በመሳሪያ የተደገፈ ግጭት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የሚገኙ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና ምሁራን እንዲፈቱ ተጠየቀ፤ የፌደራል መንግስት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊና ተፈፃሚ እንዲያደርግም ተጠይቋል።

ጥያቄዎቹ የቀረቡት በአማራ ክልል በባሕር ዳር ከተማ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ መጠናቀቁን ተከትሎ ተሳታፊዎቹ ባወጡት የአቋም መግለጫ ነው።

ባህርዳር ከተማ ሰኔ 17 እና ዛሬ ሰኔ 18/2016 ዓ.ም በተካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ ከሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እና ከአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የተውጣጡ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸው ተጠቁሟል፤ ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ትላንት ሰኔ 18 ቀን ተጠናቋል።

ተሳታፊዎቹ ካወጧቸው የአቋም መግለጫ ነጥቦች መካከልም በክልሉ ውስጥ ከተፈጠረው ችግር ጋር ተያይዞ ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ዜጎች ማለትም ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ምሁራን፣እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ዜጎች በክልሉ ውስጥ ለምንገነባው ዘላቂ ሰላም የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማስቻል መንግሥት በይቅርታና በምህረት ነፃ እንዲወጡ በማድረግ ሚናቸውንና ድርሻቸውን እንዲወጡ እንጠይቃለን የሚለው ይገኝበታል።

የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የፊደራል መንግስትና የክልላችን መንግሥት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ ያለው የኮንፈረንሱ የአቋም መግለጫ በህወሀት በኩል ገና ከጅምሩ ጀምሮ ስምምነቱን እንደ ጊዜ መግዣ በመጠቀም የማንነት እና የራስ አሥተዳደር ጥያቄ ባለባቸዉ አካባቢዎች ወረራ በመፈፀም ላይ ይገኛል ሲል ኮንኗል።

በመሆኑም መንግስት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊና ተፈፃሚ እንዲሆን በማድረግ ወራሪ ኀይሎች ከወረሩበት ቦታ በፍጥነት እንዲወጡ እንድሁም ጥያቄዎች በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ እልባት እንዲሰጣቸው ስንል የሰላም ኮንፈረንሳችን ይጠይቃል ብሏል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተጨማሪም የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ባወጡት መግለጫ ህገመንግሥትን ከማሻሻለ ጀመሮ በተለያዩ ማህበራዊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ያነሷቸውን ጥያቄዎች በየፈርጃቸው ለፌደራል መንግሥትና ለክልሉ መንግስት እንዲቀርብልን ስምምነት ላይ መደረሱን ያመለከቱበት ይገኛል።

መሳሪያ አንግበው ስለሚፋለሙ የክልሉ ታጣቂዎች ጥያቄያችሁን በሰላማዊ መንገድ በውይይትና በድርድር እንዲታቀርቡ፣ መገዳደል ይብቃን ብላችሁ ወደ ወገኖቻችሁ እንድትቀላቀሉ ጥሪ አስተላልፏል።

መንግሥትም ሆደ ሰፊ በመሆን ተፋላሚዎቹን ለሕዝቡ ሰላም ሲባል በይቅርታና በክብር እንዲቀበላቸው ጥሪ ቀርቧል።

በክልላችን ውስጥ የምትንቀሳቀሱ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ኀይሎች በሰላማዊ መንገድ ለመታገል የሚመጡ ታጣቂዎችን በፍፁም ሙያዊ ዲስፕሊንና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት አቀባበል አድርጉላቸው የሚል ጥሪም ተላልፏል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button