ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡በአማራ ክልልና አዲስ አበባ በተከሰተ የቤንዚን እጥረት 'ለከፍተኛ' እንግልት መዳረጋቸውን አሽከርካሪዎችና ነዋሪዎች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2016 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል እና በአዲስ አበባ በተከሰተ የቤንዚን እጥረት ‘ለከፍተኛ’ እንግልት መዳረጋቸውን ነዋሪዎችና አሽከርካሪዎች ገለጹ።

በአማራ ክልል መዲና ባሕር ዳር ነዋሪ የሆኑት አቶ ቶማስ ገብረማርያም፤ በክልሉ የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ የነዳጅ እጥረት ማጋጠሙን ገልጸዋል። በተጨማሪም በከተማዋ የሚስተዋለው ህገ-ወጥነትና እና የጥቁር ገበያ ንግድ መፋፋም ለእጥረቱ መንሰኤ ሊሆን ይችላል ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ አስረድተዋል።

“ባሕርዳር ከተማ ከፍተኛ የቤንዚን እጥረት አለ። የጥቁር ገበያውም በከተማዋ ልዩ ልዩ ስፍራዎች ተስፋፍቷል። ለምሳሌ በሊትር 82 ብር የሚሸጠው ቤንዚን በህገወጥ ንግዱ እስከ 180 ብር እየተሸጠ ይገኛል።” ሲሉ የገለጹት ነዋሪው አክለውም “በዚህ ህገወጥ በሆነው የነዳጅ ጥቁር ገበያ ውስጥ የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች እና አንዳንድ አሽከርካሪዎች ተሳታፊ መሆናቸውን” ጠቁመዋል።

“ለምሳሌ በሊትር 82ብር የሚሸጠውን ቤንዚን አንዳንድ ግለሰቦች ከማደያ ባለቤቶች ጋር በመመሳጠር በብዛት ከፍ ባለ ዋጋ እስከ 100 ብር ይረከቧቸውና እነዚሁ ግለሰቦች በህገወጥ ንግዱ አንዱን ሊትር ነዳጅ እስከ 180 ብር ድረስ ይሸጡታል። አንተ ቤንዚን ፈልገህ ማደያ ስትሄድ የለም ትባላለህ።”  ሲሉ ገልጸዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሌላ በባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው በከተማዋ ባጋጠመው የቤንዚን እጥረት ምክንያት የትራንስፖርት ታሪፍ ላይ በየጊዜው ጭማሪ እንደሚስተዋል ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

“ነዋሪው በከፍተኛ ምሬት ውስጥ ነው የሚገኘው። የትራንስፖርት ታሪፍ ላይ በየጊዜው ጭማሪ ይስተዋላል። በተለይ የባለ ሶስት እግር አሽከርካሪዎች በየጊዜው ዋጋ ይጨምራሉ። ምክንያት ስትላቸው ቤንዚን ጨምሯል ነው መልሳቸው። የ30 በር መንገድ እስከ 50 እና 60 ብር ያስከፍሉናል።” ሲሉ ገልጸዋል።

በጎንደር ከተማ አሽከርካሪ የሆኑት አቶ አየለ በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ የቤንዚን እጥረት እንደሚስተዋል ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በጥቁር ገበያ የምትገዛው ነዳጅ እንኳን አሁን ላይ የለም” ያሉት አቶ አየለ አክለውም አሽከርካሪው አሁን ላይ በእጥረት የተነሳ በመሰላቸት ስራ ሳይሰራ የሚያሳልፏቸው ቀኖች መኖራቸውን ተናግረዋል።

“ከዚህ ቀደም ሁለቱን ሊትር ቤንዚን በጥቁር ገበያ እስከ 300ብር እንገዛ ነበረ። አሁን ላይ እሱም የለም እየተባልን ተቸግረናል።” ያሉት አሽከርካሪው አክለውም አሁን ላይ አሽከርካሪዎች ያለ ስራ ቁጭ ብለው የሚያሳልፉበት “አሳዛኝ” ነገሮች እየተፈጠሩ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፋንታው ፈጠነ ከዶቸ ቨለ ጋር ጋር ባደረጉት ቆይታ ለቤንዚን እጥረት አንዱ ምክንያት “በክልሉ ያለው የፀጥታ እጦት” መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህም በነዳጅ ጫኞች ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን የገለጹት አቶ ፋንታው ፈጠነ አክለውም “ከሽያጭ ስርዓት ውጪ የቤንዚን ሸያጭ” መኖሩን ተናግረዋል። 

አቶ ፋንታው ችግሮቹ የተለዩ መሆናቸውን ገልጸው የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በቴክኖሎጂ የታገዘ ግብይት አለመኖሩን ጠቁመው ይህም ለብክነት በመዳረግ ለነዳጅ እጥረቱ መንሰኤ እንደሚሆን ምክትል ሃላፊው ተናግረዋል።

በተመሳሳይ መልኩ በአዲስ አበባም የቤንዚን እጥረት ያጋጠመ ሲሆን በዚህም አሽከርካሪዎች ለእንግልት መዳረጋቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

አሽከርካሪዎቹ በርካታ አካባቢዎች የሚገኙ ማደያዎች ላይ ቤንዚን የለም እየተባለ መሆኑን ገልጸዋል። በተለያዩ ስፍራዎች ነዳጅ ለመቅዳት ረጃጅም ሰልፎችን መሰለፍ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

በነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የነዳጅ ውጤቶች ስርጭት እና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሞኜ በበኩላቸው ለኢፕድ በሰጡት ምላሽ ችግሩ መስተዋሉን አምነው የማጣራት ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን አመላክተዋል።

“ለመዲናዋ በቀን እስከ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሊትር ቤንዚን ይገባላታል” ያሉት ዳይሬክተሩ አክለውም “በከተማዋ ከፍተኛ የቤንዚን ተጠቃሚ የሆኑት የባጃጅና ሞተር እንቅስቃሴ በተገደበበት ወቅት በማደያዎች የቤኒዚን እጥረት ለምን እንደተከሰተ የማጣራት ስራ ይሰራል።” ሲሉ ገልጸዋል።

በተጨማሪ የተፈጠረውን የቤንዚን እጥረት ለመቀነስ ከሱሉልታ መጠባበቂያ ዲፖ 20 ቦቲ ቤንዚን በአዲስ አበባ ከተማ ሁሉም አካባቢዎች መከፋፈሉን ገልጸዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button