ዜናፖለቲካ

ዜና፡ “መሮ ለሰላም ቁርጠኝነት አሳይቶ የእኔ መንግሥት ግን ሰላሙን አደናቀፈ”- አቶ ታዬ ደንደአ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 27/2016 ዓ.ም፡- የዳሬሰላሙ ድርድር እንዳይሳካ ያደረገው መንግሥት ነው ብዬ አምናለሁ ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ እና የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ) አባል የሆኑት አቶ ታዬ ተናገሩ። አገሪቷን በሚያስተዳድረው የብልጽግና ፓርቲ ውስጥ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው እያገለገሉ ያሉት አቶ ታየ ደንደአ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ “መሮ ለሰላም ቁርጠኝነት አሳይቶ የእኔ መንግሥት ግን ሰላሙን አደናቀፈ” ሲሉ መናገራቸውን አስነብቧል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን የሚመራው ጃል መሮ፣ መንግሥት ከፈለገ ይግደለኝ ብሎ፣ መንግሥት በሚቆጣጠረው የአየር ክልል ውስጥ አልፎ፣ ወደ ታንዛኒያ በአውሮፕላን መሄዱ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ነው የሚያሳየው ብዬ አምናለሁ”  ሲሉ አቶ ታዬ ነግረውኛል ያለው ቢቢሲ የኦሮሞ ፖለቲካ ችግር አሁን ያለበት ቦታ ከደረሰ እና ሁለቱ ወገኖች ልዩነታቸው በሰላም እንዲፈታ ከወሰኑ በኋላ “ይህ የሰላም ድርድር እንዲደናቀፍ ያደረገው እኔ ያለሁበት መንግሥት ነው” ማለታቸውንም አመላክቷል።

“እኔ ያለሁበት መንግሥት ‘ችግር ውስጥ ነን፤ ተወያይተን መፍትሄ እናመጣለን’ ብዬ ስጠይቅ ቤቱ ለውይይት ክፍት አይደለም በማምታታት እና በማደናገር ማለፍ ነው የሚፈለገው። የእኔ መንግሥት እንዲህ ዓይነት ጸባይ ነው ያለው” ሲሉ መንግስታቸውን መተቸታቸውን ዘገባው አካቷል።

በታንዛኒያ ድርድሩ ተጀምሮ በሁለተኛው ቀን፣ ከመንግሥት ወገን ፕሮፓጋንዳ መንዛት እንደተጀመረ የሚገልጹት አቶ ታዬ “ሸኔን አጥፍተናል፣ አከርካሪውን ሰብረናል የሚል ፕሮፓጋንዳ ተጀመረ። ፕሮፓጋንዳ ብቻ ሳይሆን ጦር ከያለበት ተንቀሳቅሶ በአምስት ዓመት ውስጥ ያላለቀው ጦርነት በድርድሩ ጊዜ ለመጨረስ፣ እንቅስቃሴ ተደረገ” በማለት ከመንግሥት ወገን ለሰላም ፍላጎት አለመኖሩን ያስረዳሉ ብሏል።

በፓርቲያቸው ውስጥ መመካከር ከቀረ በኋላ የኦሮሞ ፖለቲካ አንድ ከመሆን ወደ መበታተን ማምራቱን ነገሩኝ ያለው ቢቢሲ በኦሮሞ ፖለቲካ ሜዳ ውስጥ በተፈጠረው ግራ መጋባት፣ ሌሎች ወደ ጫካ እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ የሕዝቡ ሰቆቃ በማምታታት ሥልጣናቸውን ማራዘም ለሚፈልጉት ትልቅ ዕድል ፈጠረላቸው ሲሉ መኮነናቸውን አካቷል።

ኦሮሚያ በአሁን ሰዓት ጦርነት ውስጥ መሆኗን የተናገሩት አቶ ታዬ፣ በዚህ ጦርነት ውስጥ ሕዝብ ለከፋ ሰቆቃ መዳረጉን ገልጸዋል።

“ሕዝባችን ባለፉት አምስት ዓመታት ይሞት ነበር። ስንት እንደሞተም በቁጥር አይታወቅም። በጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በእስራኤል ስንት አንደሞተ፣ ከፍልስጤም ስንት አንደሞተ በቁጥር ይታወቃል። በኦሮምያ ያለው እልቂት ግን የሚታወቅ ነገር የለም።”

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በዳሬሰላም የነበረው የሰላም ድርድር ከፈረሰ በኋላ የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ “ሰላምን እምቢ ያለ አካል ተገዶ ወደ ሰላም እንዲመጣ እርምጃ እየተወሰደበት ነው ሲል መግለጫ አውጥቶ ነበር፣ ይህ መግለጫ በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል ያለው ችግር በጦርነት ለመፍታት እየተሄደበት መሆኑን የሚገልጽ ነው ሰሉ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል ያለውዘገባው “ሰዎቹ [ታጣቂዎቹ] ጊዳሚ እያሉ መፍትሄ ያላመጣ ጦር አሁን ሱሉልታ ከደረሱ በኋላ ችግሩን አይፈታም” በማለት ሃሳባቸውን መግለጻቸውን አስታውቋል።

“ከዚህ ቀደም ይህ ጦር በቄለም ወለጋ ውስጥ በአንድ ወይንም በሁለት ወረዳ ውስጥ ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እየተዋጋን ነው። ስለዚህ ይህ ጦር ችግሩን አልፈታም ማለት ነው። አሁን ደግሞ ተስፋፍቶ ይህ ጦር የሌለበት ዞን የለም ማለት ትችላለህ። አሁን አንዲያውም እዚህ ቅርብ ሱልልታ ነው ያለው” በማለት ጦርነት መፍትሄ አንዳልሆነ እና እንዳላመጣ ምልከታቸውን መግለጻቸውንም አካቷል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button