ዜናቢዝነስ

ዜና፡ በቴሌ ብር አማካኝነት በየቀኑ ቢያንስ የአምስት ቢሊዮን ብር የገንዘብ ዝውውር ይደረጋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 24/2016 .ም፡ የቴሌ ብር አገልግሎት ወደ ሥራ ከገባ ጊዜ ጀምሮ አንስቶ አንድ ነጥብ ስድስት ትሪሊዮን ብር ዝውውር መደረጉን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ። በቀን የአምስት ቢሊዮን ብር ዝውውር እንደሚደረግም የኩባንያውን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩን ዋቢ በማድረግ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።

25 ባንኮች ከቴሌ ብር ጋራ ገንዘብ ዝውውር በማድረግ በትስስር እየሰሩ ይገኛሉ ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል ያለው ዘገባው በዚህም የየዕለት የገንዘብ ዝውውሩ ሲታይ በቀን አምስት ቢሊዮን ብር ማለት ነው ማለታቸውን ጠቁሟል።

በቀን ዝውውር ከሚደረገው የገንዘብ መጠን 19 በመቶ የሚሆነው ከሌሎች ባንኮች ወደ ቴሌ ብር የሚገባ መሆኑን፤ 21 በመቶ የሚሆነው ከቴሌ ብር ወደ ሌሎች ባንኮችና የዲጂታል ፋይናንሲንግ አማራጮች የሚዘዋወር መሆኑን አስረድተዋል ብሏል።

ከአጠቃላዩ የገንዘብ ልውውጥ 42 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ በኢ-ብር ግብይት ላይ ይውላል ሲሉ ተናግረው ያለው ዘገባው ይህም ኢኮኖሚን ከገንዘብ ንክኪ ነጻ በሆነ መንገድ ለመገንባት ያለው ሚና የጎላ ነው ማለታቸውን አስታውቋል።

አሠራሩ ጥሬ ገንዘብ ማሳተም ሳያስፈልግ በዲጅታል ፋናንሲንግ ብቻ ለመጠቀም እድል እየፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል ያለው ዘገባው  ከቁጠባ ሂሳብ አንጻርም በአንድ ዓመት ውስጥ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ደንበኞች 7 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የቁጠባ ሂሳብ ተንቀሳቃሽ አድርገዋል ማለታቸውን አካቷል።

ኢትዮ ቴሌኮም 73 ሚሊዮን ደንበኞች እንዳሉት አመላክተው፤ ደንበኞቹ ስልክ ከመደወል እና መልዕክት ከመላክ ያለፈ በስልካቸው አማካኝነት በርካታ ተግባራትን እንዲከውኑ ለማስቻል አዳዲስ ሥራዎች በቀጣይ እንደሚከናወኑ መናገራቸውንም አስታውቋል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button